በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች 1,919 ቀበሌዎች “በጠላት” ተይዘው እንደነበር ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት አስታወቀ። የደህንነት ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል አካባቢ ያሉ የስጋት ሁኔታዎች “ከጸጥታ አካላት አቅም በታች” ናቸው ብሏል።
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 2፤ 2014 ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ነው። ከሁለት ወራት በፊት ሰኔ 1፤ 2014 ባካሄደው ስብሰባ ወቅት “በአስቸኳይ ለማከናወን ተወስነው የነበሩ ተግባራትን” በመግለጫው የዘረዘረው ምክር ቤቱ፤ ከእነዚህ መካከል “አሸባሪና የታጠቁ ቡድኖችን፤ በአመራራቸው ላይ ትኩረት በማድረግ መደምሰስ” የሚለው አንዱ እንደነበር ጠቅሷል።

በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ክልል በተወሰደው እርምጃ፤ “በጠላት ተይዘውና ፈርሰው ነበር” ከተባሉ 1,739 ቀበሌዎች ውስጥ 1,255 ያህሉን እንደገና ማደራጀት እንደተቻለ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ገልጿል። በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን “ሸኔ” የተሰኘውን ቡድን “ለመደምሰስ” ሶስት ኮማንድ ፖስቶች መዋቀራቸውንም አክሏል።
በሸዋ፣ በወለጋ እና በጉጂ በተቋቋሙት በእነዚህ ኮማንድ ፖስቶች አማካኝነት፤ በአካባቢዎቹ “የተቀናጀ ስምሪት” በመካሄድ ላይ መሆኑን የደህንነት ምክር ቤቱ በመግለጫው አስፍሯል። የመከላከያ ሰራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል አመራር እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በጋራ አካሄደዋቸዋል በተባሉ በእነዚህ ስምሪቶች፤ 3,180 የሸኔ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምክር ቤቱ አስታውቋል።
የደህንነት ምክር ቤቱ “እጃቸውን ላለመስጠት አሻፈረኝ ያሉ” በማለት የገለጻቸው ታጣቂዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን በመግለጫው ቢጠቅስም፤ ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ ግን በቁጥር አላስቀመጠም። በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ “ሕገ ወጥ ታጣቂዎች” መገደላቸው በመግለጫው ተነስቷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 1,826 የሚደርሱ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና “እጃቸውን በሰላም የሰጡ ሕገ ወጥ ታጣቂዎች” ደግሞ ወደ መደበኛ ሕይወት የማስገባት ስራ መከናወኑ በደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ ላይ ሰፍሯል። በክልሉ 180 ቀበሌዎች “ጠላት” ከተባሉ ኃይሎች “ነጻ መውጣታቸውን” ያስታወቀው የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ፤ ከእነዚህ ውስጥ በ169ኙ ላይ “የመንግስት መዋቅር መልሶ ተደራጅቷል” ብሏል።
በብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ የዛሬ ስብሰባ ላይ ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተጨማሪ የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሌ ክልሎች እና የአዲስ አበባ ከተማ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎች መገምገማቸው ተገልጿል። በትግራይ ክልል ያለውን “የስጋት ሁኔታ ከቀረበለት ሪፖርት በመነሳት” መገምገሙን የገለጸው የደህንነት ምክር ቤቱ፤ በግምገማውም በክልሉ ያሉ “ሁኔታዎች ከጸጥታ አካላት አቅም በታች መሆናቸውንና በተገቢው መንገድ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን” ማረጋገጡን በመግለጫው አመልክቷል።
የደህንነት ምክር ቤቱ ከዚህ ግምገማ በመነሳት “በአመራሩና በጸጥታ አካላት ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራት በመለየት አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ” በመግለጫው ላይ ቢነሳም፤ የአቅጣጫዎቹ ዝርዝር ምንነት ግን አልተብራራም። ሆንም ምክር ቤቱ፤ በጸጥታ እና ደህንነት ረገድ ታይተዋል ያላቸውን ድክመቶች ባነሳበት የመግለጫው ክፍል፤ “በተገቢው ትኩረትና ቁርጠኝነት ካልተሰሩ” አሁን ያለው “አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ” የማይሆንባቸው ያላቸውን ተግባራት ዘርዝሯል።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ “የጸጥታና ደህንነት መዋቅሩ በሚጠበቀው መጠን አለመጥራት” የሚለው ይገኝበታል። የደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ በድክመትነት ያነሳው ሌላው ነጥብ “ጁንታ” በሚል ከጠራው ኃይል ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ኃይል “ከውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጋር ሊያደርገው የሚፈልገውን ቅንጅት ለማምከን በልኩ አልተሰራም” ብሏል የምክር ቤቱ መግለጫ። “የአመራሩን እና የሕዝቡን የጸና ሥነ ልቡና የመገንባት ስራም” በተመሳሳይ መልኩ “በተገቢው ልክ አለመሰራቱን” ምክር ቤቱ በመግለጫው አንስቷል።
“በየጊዜው የምናደርጋቸው የግምገማ ውይይቶች፣ አዳዲስ ምክንያቶችን የምንሰማባቸው ሳይሆኑ፣ የችግሮችን መቀነስና የሰላምና ደህንነትን መስፈን የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው” ያለው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ፤ “ይህ ደግሞ የሚሳካው ዕቅድን በሚገባ በመገንዘብ፣ የሚያስፈልገውን ስምሪት በማካሄድና እስከ መጨረሻው ድረስ ለውጤቱ ብቻ በመድከም ነው” ሲል አሳስቧል።
በ1994 ዓ.ም. በወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት፤ ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ምንጭ የሆኑ ሁኔታዎችን በመገምገም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ሃሳብ የማቅረብ ኃላፊነት ያለው ነው። ምክር ቤቱ ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚመለከቱ የአፈጻጸም መመሪያዎችን የማመንጨት ተጨማሪ ኃላፊነትም ተጥሎበታል።

የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በሚያዝዘው መሰረት የተቋቋመውን የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በሰብሳቢነት የሚመራው በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆኑ በማቋቋሚ ደንቡ ላይ ተደንግጓል። ሰባት ቋሚ አባላት ያሉት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸውን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹሙን፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩን እንደዚሁም የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሩን ያቀፈ ነው። ከእነርሱ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የምክር ቤቱ አባል እና ጸሃፊ በመሆን ተካትተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)