በካፋ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት በአካባቢው ሰራዊት ሊሰማራ ነው

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት “በወሳኝ ቦታዎች ሰራዊት ለማስገባት” የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ አስታወቁ። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለጹት ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 3 መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ለጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ነው።

ዶ/ር ነጋሽ ለምክር ቤቱ አባላት በንባብ ያቀረቡት ሪፖርት የአዲሱን ክልል ያለፉትን ሰባት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የዳሰሰ ነበር። የስራ አፈጻጸማቸው በሪፖርቱ ከተካተቱ ዘርፎች ውስጥ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ይገኝበታል። በ2014 በጀት ዓመት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማስፈን በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል “ከጥቂት አካባቢዎች በስተቀር አንጻራዊ ሰላም ያለበት” መሆኑን ጠቁመዋል። 

በካፋ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚከሰቱ ዘረፋዎችን እና ግድያዎችን ለማስቆም፤ በበጀት ዓመቱ እቅድ ተይዞ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ዶ/ር ነጋሽ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። በሶስቱ ዞኖች ያሉ የጸጥታ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ተከታታይ ውይይቶች መካሄዳቸውንም አስረድተዋል።

ክልሉ “ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች” ጋር በተያያዘ በአካባቢዎቹ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶችን እያደረገ በሚገኝበት ወቅት፤ በኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ወረዳዎች የከብት ዝርፊያ እና ግድያ መፈጸሙን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። ይህን ክስተት ተከትሎም ክልሉ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማወያየት “ወንጀለኞችን የመለየት እና ንብረት የማስመለስ ስራ” መስራቱን ዶ/ር ነጋሽ ገልጸዋል። “በዚህም የተወሰኑ ከብቶችን የማስመለስ ስራ ተሰርቷል” ብለዋል።

በቀጠናው ለሚስተዋሉትን የጸጥታ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፍጠር “መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት ቁጥጥር ለማድረግ” መታሰቡን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አመልክተዋል። በኮንታና ካፋ ዞኖች ወሳኝ በሆኑ ቦታዎች ላይም ሰራዊት ለማስገባት የቅደመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ዶ/ር ነጋሽ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)