በሃሚድ አወል
በደቡብ ክልል ስር ከሚገኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ውስጥ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ባለማጽድቅ ብቸኛ የሆነው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት፤ አስቸኳይ ጉባኤውን ነገ ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 ሊያካሄድ ነው። የአስቸኳይ ጉባኤውን መጠራት የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አርሽያ አህመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባላት፤ በነገው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደተላለፈላቸው ገልጸዋል። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት 97 አባላት ያሉት ሲሆን ከእነርሱ ውስጥ ስድስቱ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተመራጮች ናቸው። ቀሪዎቹ የምክር ቤት አባላት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩ እና ምክር ቤቱን የተቀላቀሉ ናቸው።
ከዚህ በፊት በነበረው ልማድ ጉባኤው ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የጉባኤውን አጀንዳዎች በያዘ ደብዳቤ ጥሪ ይደረግላቸው እንደነበር የሚያስታውሱት የምክር ቤት አባላት፤ የአሁኑ ስብሰባ አጀንዳ ግን እንዳልተገለጸላቸው ተናግረዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የዞኑ ምክር ቤት አባል፤ የነገው አስቸኳይ ጉባኤ ዋና አጀንዳ “የአደረጃጀት ጉዳይ” ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የነገው ጉባኤ ዋና አጀንዳ ምን እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፤ “አጀንዳ ለምክር ቤት አባላት ብቻ ነው የሚገለጸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከሳምንት በፊት ጉባኤዎቻቸውን ባካሄዱ የደቡብ ክልል ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ዋነኛ አጀንዳ የነበረው፤ በገዢው ፓርቲ የቀረበው አዲስ የክልል አደረጃጀት ነበር።
የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለውን ይህን የገዢውን ፓርቲ የውሳኔ ሃሳብ፤ 10 ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች በየምክር ቤቶቻቸው አጽድቀዋል። የየምክር ቤቶቹ አፈ ጉባኤዎች ይህንኑ ውሳኔያቸውን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 28፤ 2014 ለፌደሬሽን ምክር ቤት አስገብተዋል። በዚሁ ይፋዊ የሰነድ ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ፤ የሁለት አዳዲስ ክልሎች ምስረታን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያስፈጽም በዞኖቹ እና ልዩ ወረዳዎች ጥያቄ ቀርቦለታል።
ከሁለቱ አዳዲስ ክልሎች መካከል አንደኛውን ለመመስረት በምክር ቤቶቻቸው የወሰኑት ዞኖች፤ የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ እና ኮንሶ ዞኖች ናቸው። የአማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶችም ይህንኑ አዲስ ክልል ለመቀላቀል ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፈዋል።

ሁለተኛውን ክልል በጋራ ለመመስረት የወሰኑት ደግሞ ሀድያ፣ ስልጤ፣ ሀላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ናቸው። ሁለተኛውን ክልል ይመሰረታሉ ከተባሉ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ጉባኤውን ያላካሄደው እና እስካሁንም ውሳኔውን ያላሳወቀው የጉራጌ ዞን ብቻ ነው።
የጉራጌ ዞንን በአጎራባች ከሚገኙ አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር በአንድ “በክላስተር” በክልል የማደራጀቱ የውሳኔ ሀሳብ ከጉራጌ ፖለቲከኞች እና “አክቲቪስቶች” ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። የውሳኔ ሃሳቡ ተቃዋሚዎች፤ የጉራጌ ዞን “ራሱን ችሎ ለብቻው በክልልነት ሊደራጅ ይገባል” የሚል አቋም አላቸው።
ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲያንጸባርቁ የቆዩት ወገኖች፤ ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 3፤ 2014 በዞኑ ዋና ከተማ ወልቄጤ የስራ ማቆም አድማ ጠርተው ነበር። ይህን ተከትሎም ትላንት ከረፋድ ጀምሮ የከተማይቱ የንግድ እንቅስቃሴ ቆሞ እንደነበር የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ እና አክቲቪስት አድማው የተጠራው “በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር” መሆኑን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)