አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የበጀት እጥረት “ትልቅ ችግር” እንደፈጠረበት አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

ከደቡብ ክልል ተነጥሎ ራሱን የቻለ ክልል ከሆነ ዘጠኝ ወራትን ያሳለፈው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ በበጀት ውስንነት ምክንያት “ትልቅ ችግር” እንዳጋጠመው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ። የክልሉ መንግስት ያጋጠመው የበጀት ጫና፤ የአዳዲስ ሰራተኞችን ቅጥር ጭምር እንዲያቆም አስገድዶታል ተብሏል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለጹት፤ በክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 3 በሰጡት ማብራሪያ ነው። ያለፉት ሰባት ወራት የክልሉ መንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ተከትለው የቀረቡት አብዛኞቹ የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች፤ ከመንገድ እና ድልድይ ግንባታዎች እንዲሁም ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ነበሩ። 

የምክር ቤቱ አባላት በተደጋጋሚ ላነሷቸው የመሰረት ልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፤ “በመንገድ፣ በድልድይ እና በውሃ በኩል የሚስተዋለው ትልቁ ችግር የበጀት ውስንነት ነው” ብለዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስር ባሉ ዞኖች ያለው አጠቃላይ የመንገድ መሰረት ልማት ስርጭት “በጣም ዝቅተኛ” መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሽ፤ በፌደራል መንግስትም ሆነ በክልሉ የመንገዶች ባለስልጣን እየተሰሩ ያሉ መንገዶች ግንባታቸው ከተጀመረ ረጅም ዓመታት በማስቆጠሩ በአሁኑ ወቅት በጀታቸው “በጣም ከፍተኛ” መሆኑን ገልጸዋል።

“እነዚህ የዛሬ ሰባት ዓመት እና ስምንት ዓመት የተጀመሩት አሁን እንደገና እናስጀምር ስንል፤ አንዳንዶቹ ሁለት እጥፍ፤ ሶስት እጥፍ ከፍ ብለዋል። የበጀት ጫናው ቀላል አይደለም። በዚህ ዓመት በክልል ማዕከል ለሚሰራ ስራ ያጸደቅነው አጠቃላይ መደበኛ እና ካፒታል በጀት 1.2 ቢሊዮን ብር ነው። እርሷን ወስደን ነው እነዚህን ስራዎች ተሟሙተን፤ ካለን ከመደበኛ ወጪያችንም ቆጥበን ወደ ነዳጁ ወደ ሌሎቹ አድርገን ስራ የሰራነው” ሲሉ ዶ/ር ነጋሽ አብራርተዋል። 

አዲሱ ክልል ያለበትን የአቅም ውስንነት ለመገንባት እና ተቋም ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ የበጀት ውስንነት “ማነቆ” ሆኖ እንደያዘው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ በመሰረት ልማት ዘርፍ ላይ ያሉትን ፕሮጀክቶች ከነባሩ የደቡብ ክልል ጋር በመሆን የመለየት ስራዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል። አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ከ70 እስከ 80 በመቶ ደርሰው የቆሙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ አፈጻጸማቸው ከ20 በመቶ ያልዘለሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

እንደ መንገድ ግንባታ ሁሉ በክልሉ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ ረገድ ያለው ትልቁ ችግር የበጀት እጥረት እንደሆነ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተነስቷል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት የማሻ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ነው። ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 318 ሚሊዮን ብር መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ነጋሽ፤ በክልሉ ስር ላሉ ስድስት ዞኖች የውሃ ፕሮጀክቶች የተመደበው አጠቃላይ ገንዘብ ግን 70 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ብለዋል።

በክልሉ ምክር ቤት አባላት ዘንድ ተደጋግሞ የተነሳው የቦንጋ ከተማ የውሃ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ያላገኘውም በተመሳሳይ ምክንያት መሆኑ በጉባኤው ላይ ተገልጿል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ እንድትሆን ለታጨችው ቦንጋ ከተማ፤ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ኮንትራት የተሰጠው ለደቡብ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ቢሆንም ስራው ከፍተኛ መጓተት አሳይቷል ተብሏል። 

“የቦንጋን [ጉዳይ] እንደ አንድ ባለሙያም እንደ አንድ ክልሉን እንደሚመራ አካልም ለዚህ ለተከበረው ምክር ቤት ደግሜ ደጋግሜ ሳነሳ ይሰማኛል” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ችግሩን ለመፍታት በደቡብ ክልል በኃላፊነት ቦታ ላይ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ጥረቶች ቢያደርጉም በዘላቂነት መፍትሔ መስጠት አለመቻላቸውን አምነዋል። “በዚህም በጣም አፍራለሁ” ሲሉም ለምክር ቤት አባላቱ ተናግረዋል። 

የቦንጋ ከተማ የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት በጀት የተመደበለትም ሆነ የሚሰራው በፌደራል መንግስት አማካኝነት ቢሆንም፤ ክልሉ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በተመለከተ ቅርብ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ዶ/ር ነጋሽ ገልጸዋል። ለውሃ ፕሮጀክቱ መጓተት መንስኤ ነው ከተባለው ከደቡብ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር የተገባው ውል እንዲቋረጥም ክልሉ ከሰሞኑ የደብዳቤ ልውውጦች እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)