ኢዜማ፤ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያን የወሰን ማካለል ውሳኔን በዚህ ወቅት ማድረግ “ከፍተኛ ስህተት ነው” አለ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን የማካለል ውሳኔን “በኃይል ለመጫን የሚደረግ ሙከራ” ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል አለ። ውሳኔውን ከአግባብነቱ እና ጊዜውን ካለመጠበቁ አንጻር “ከፍተኛ ስህተት” ሆኖ ማግኘቱን ፓርቲው አስታውቋል። 

ኢዜማ ይህን የገለጸው የፓርቲው የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዚሁ ስብሰባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት የአስተዳደር ወሰን ለማካለል የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን እንደተረዳ ገልጿል። 

በኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሀገራዊ ምክክር ላይ ይፈታሉ ብሎ ከሚጠበቃቸው ጉዳዮች መካከል  አንዱ “የአስተዳደር አከላለል” መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤ ከሰሞኑ እየተሰሙ ያሉ የአስተዳደር ወሰን ማካለል እና የ“ክላስተር” አደረጃጀት ውሳኔዎች ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለችበትን “ከፍተኛ ችግር ታሳቢ ያላደረጉ ናቸው” ሲል ተችቷል።

“ጉዳዩን የምናየው ‘ማን ምን አገኘ? ማንስ ምን አጣ?’ በሚል ቁንጽል እሳቤ ሳይሆን፤ ከአግባብነቱ እና ጊዜውን ካለመጠበቁ አንጻር ከፍተኛ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል። በፍጥነት ሊታረም እንደሚገባም ልናሳስብ እንወዳለን” ሲል ኢዜማ ገልጿል።

የአስተዳደር ወሰን ማካለሉ መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጠቃሚ መሆኑን ያመለከተው ፓርቲው፤ ይህን የተመለከቱ ውሳኔዎችን ማስተግበር የሚቻለው ዜጎችን አሳትፎ የሂደቱ ባለቤት በማድረግ መሆኑን አስታውቋል። ውሳኔዎቹ በሚመለከታቸው አካባቢዎች እየኖረ ያለው ህዝብ “የመንግሥትን ውሳኔዎች የመቀበል ግዴታ የሚኖርበት፤ እንደ ዜጋ ሂደቱን የማወቅ እና የመሳተፍ መብቱ ሲከበርለት ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲልም ኢዜማ አሳስቧል።

“[የአስተዳደር ወሰን የማካለል ውሳኔን] የምናየው ‘ማን ምን አገኘ? ማንስ ምን አጣ?’ በሚል ቁንጽል እሳቤ ሳይሆን፤ ከአግባብነቱ እና ጊዜውን ካለመጠበቁ አንጻር ከፍተኛ ስህተት ሆኖ አግኝተነዋል። በፍጥነት ሊታረም እንደሚገባም ልናሳስብ እንወዳለን”

– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልል መንግስት መካከል ተደረሰበት የተባለው የወሰን ማካለል ስምምነት  ዝርዝር በቀጣይ “በጥልቀት የሚጣራ” መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል። የወሰን ማካለል ስምምነቱን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ በኦሮሚያ ክልል መንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የወጣ መረጃ የለም። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)