የህዳሴ ግድብ በሁለት ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ተናገሩ

በሃሚድ አወል

የታላቁ ህዳሴ ግድብ እስከ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ። የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት 83.3 በመቶ መድረሱን አቶ ክፍሌ ገልጸዋል።

የግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን የኤሌክትሪከ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ በተበሰረበት ስነ ስርዓት ላይ ነው። በዚህ ስነ ስርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች እና የጦር መኮኖንች ተገኝተዋል። 

አቶ ክፍሌ በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር “በሚቀጥሉት ሁለት ወይም ሁለት ተኩል ዓመታት ግድቡን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ፣ በየደረጃው ሙሌት በማከናወን፣ ቀሪ ዩኒቶችን በመትከል እስከ 5,150 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው” ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት የህዳሴው ግድብ የሲቪል ስራዎች ግንባታ 95 በመቶ፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎቹ ደግሞ 61 በመቶ መድረሳቸውን ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። የግድቡ ውሃ ማስተላለፊያ እና ብረታብረት ስራዎች የስራ ክንውንም 73 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። በግድቡ ፕሮጀክት ላይ በተደረገ ማስተካከያ፤ በሶስት ዓመታት ውስጥ በግድቡ ውስጥ የነበረባቸው የውሃ ማስተላለፊያ የብረታብረት ስራዎችን በማጠናቀቅ፤ የመካከለኛውን የግድብ ከፍታ ከ25 ሜትር ወደ 100 ሜትር ማድረስ መቻሉንም አክለዋል።

በ2014 በህዳሴ ግድብ ለማከናወን ከተያዙ አብይ እቅዶች ውስጥ “በሁለት ተርባይንና ጀነሬተሮች ኃይል ማመንጨት” የሚለው እንደሚገኝበት ያስታወሱት አቶ ክፍሌ፤ “ይህ እቅድ ተሳክቶ በሁለቱም ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት ተችሏል” ብለዋል። አቶ ክፍሌ አክለውም ሶስተኛው ዙር ህዳሴ ግድብ ሙሌት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የግድቡ የመጀመሪያው ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረው ከስድስት ወራት በፊት የካቲት አጋማሽ ላይ ነበር። ዛሬ ኃይል ማመንጨት የጀመረው እንዲሁም የመጀመሪያው ተርባይንም እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የኃይል መጠን ያመነጫሉ። የህዳሴው ግድብ በአጠቃላይ 13 ተርባይኖች ይኖሩታል።

በዛሬው የሁለተኛው ተርባይን የኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብን ተጠቅማ “ኢኮኖሚያዋን በማሻሻል እና በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ብርሃን እንዲያገኙ ከመፈለግ ውጭ”፤ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን “የመግፋትም ሆነ የመጉዳት ዓላማ” እንደሌላት አስታውሰዋል። ግብጽ እና ሱዳን የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌትን ጨምሮ በአጠቃላይ የግንባታው ሂደት ላይ ተቃውሟቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው ንግግራቸው ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በግድቡ ላይ ያላቸውን ስጋት በድርድር እና በንግግር እንዲፈቱ ጠይቀዋል። “ከዚያ ውጭ ያለው ማንኛውንም አማራጭ የጀመርነውን ነገር የማያስቆም እንዲሁ በከንቱ የሚያደክም መሆኑን ተገንዝበው፤ ወደ ሰላም ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)