የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በክላስተር ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አደረገ

በሃሚድ አወል

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ባካሄደው አስቸካይ ጉባኤ፤ በደቡብ ክልል ስር ከሚገኙ ሌሎች የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር በ“ክላስተር” ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ አደረገ። የጉራጌ ዞንን ከሌሎች አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር በማዳመር የጋራ ክልል ለመመስረት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፤ 52 የምክር ቤት አባላት ተቃውመታል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት 97 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ከእነርሱ ውስጥ 91 ያህሉ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ምክር ቤቱን የተቀላቀሉ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ስድስት አባላት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ተመራጮች ናቸው። ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 በተካሄደው የዞኑ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ከተገኙ 92 የምክር ቤት አባላት መካከል 40ዎቹ ውሳኔውን ደግፈው ድምጽ መስጠታቸውን የጉባኤው ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፎቶ፦ የጉራጌ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የተዘጋጀውን የክላስተር የክልል አደረጃጀት ምክረ ሃሳብ በንባብ ያሰሙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ነበሩ። አስተዳዳሪው ምክር ሃሳቡን ካሰሙ በኋላ በጉባኤው የተገኙ አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

ከምክር ቤት አባላቱ በብዛት የተነሱ አስተያየቶች “ጥያቄያችን ህገ መንግስታዊ ነው”፣ “የምንጠብቀው የፌደሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ነው” የሚሉ እንደነበሩ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል። በጉባኤው አስተያየታቸውን የሰጡ የምክር ቤት አባላት፤ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ህዳር 17፤ 2011 ዓ.ም. ባደረገው ጉባኤ ዞኑ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ ውሳኔ ማሳለፉን በተደጋጋሚ ይጠቅሱ ነበር ብለዋል። 

“ቀድመን የወሰነው ውሳኔ መከበር አለበት። ህዝቡ በፍጹም በክላስተር የመደራጀት ሃሳብ የለውም” የሚል አስተያየት ከዞኑ ምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ ይሰማ እንደነበር እኚሁ የጉባኤው ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የምክር ቤት አባላቱ ላነሷቸው አስተያየቶች፤ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል “ሰፊ ማብራሪያ” መስጠታቸውንም አክለዋል። 

ፎቶ፦ የጉራጌ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

በአስቸኳይ ጉባኤው ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ “በክልልነት መደራጀት ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ ነው። ነገር ግን አሁን [በክላስተር የመደራጀት] ሀሳቡን እንቀበል” ሲሉ ጥያቄ ማቅረባቸውን የጉባኤው ተሳታፊዎች አስረድተዋል። ሆኖም ጥያቄያቸው በበርካታ የገዢው ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ጭምር ተቀባይነት ሳይገኝ ቀርቷል።  

የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለውን እና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበውን አዲስ የክልልነት አደረጃጀት በምክር ቤቱ ባለማጽደቅ ጉራጌ ዞን ብቸኛው ሆኗል። ቀሪዎች የደቡብ ክልል 10 ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ውሳኔውን በምክር ቤቶቻቸው ባካሄዱት ጉባኤ ማጽደቃቸው ይታወሳል። 

የምክር ቤቶቹ አፈ ጉባኤዎች ይህንኑ ውሳኔያቸውን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 28፤ 2014 ለፌደሬሽን ምክር ቤት ማስገባታቸው ይታወሳል። የፌደሬሽን ምክር ቤት የሁለት አዳዲስ ክልሎች ምስረታን እንዲያስፈጽም በዞኖቹ እና ልዩ ወረዳዎች ጥያቄ ቀርቦለታል። 

ከሁለቱ አዳዲስ ክልሎች መካከል አንደኛውን ለመመስረት በምክር ቤቶቻቸው የወሰኑት ዞኖች፤ የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ እና ኮንሶ ዞኖች ናቸው። የአማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ እና አሌ ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶችም በተመሳሳይ ይህንኑ ውሳኔ አሳልፈዋል።

ሀድያ፣ ስልጤ፣ ሀላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ደግሞ ሁለተኛውን ክልል በጋራ ለመመስረት የሚያስችላቸውን የውሳኔ ሃሳብ በየምክር ቤቶቻቸው አጽድቀዋል። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የ“ክላስተር” አደረጃጀቱን ቢያጽድቀው ኖሮ የሚቀላቀለው ይህንኑ ሁለተኛ ክልል ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)