በሃሚድ አወል
በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ስር የሚገኘው የማረቆ ወረዳ ምክር ቤት፤ በ“ክላስተር” አደረጃጀት ላይ የራሱን አቋም ለመያዝ ለነገ ቅዳሜ ነሐሴ 7፤ 2014 አስቸኳይ ጉባኤ ጠራ። የወረዳው ምክር ቤት በነገው አስቸኳይ ጉባኤው፤ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን የሚደግፍ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን በ16 ወረዳዎች እና በስምንት የከተማ አስተዳደር የተዋቀረ ሲሆን በስሩ ሶስት ብሔረሰቦችን ይዟል። በዞኑ ውስጥ ዕውቅና ያላቸው ያሉት ሶስት ብሔረሰቦች ጉራጌ፣ ማረቆ እና ቀቤና ናቸው። የማረቆ ብሔረሰብ በጉራጌ ዞን ውስጥ በወረዳ ደረጃ የተዋቀረ ሲሆን፤ በዞኑ ምክር ቤት ውስጥ አምስት መቀመጫዎች አሉት።
በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበው እና የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለው የ“ክላስተር” አደረጃጀት ምክረ ሃሳብ በማረቆ ወረዳ ለውይይት በቀረበበት ወቅት ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ እንደነበር አንድ የወረዳው አመራር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በጉራጌ ዞን ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው አምስት የማረቆ ወረዳ ተወካዮችም፤ ይህንኑ ድጋፋቸው በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የዞኑ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ጭምር ማንጸባረቃቸውን አስረድተዋል።

ትላንት ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 በተካሄደው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ከተገኙ 92 አባላት ውስጥ 40ዎቹ ለ“ክላስተር” አደረጃጀት ምክረ ሃሳብ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ሆኖም ምክረ ሃሳቡ ከ52 አባላት ተቃውሞ ስለገጠመው፤ በአብላጫ ድምጽ አሰራር መስረት በጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውድቅ ተድርጓል።
የማረቆ ወረዳ ይህንን የዞኑን ውሳኔ ባለመቀበሉ ሳቢያ የነገውን አስቸኳይ ጉባኤ እንዲጠራ ማድረጉን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማረቆ ወረዳ ምክር ቤት አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የነገውን የጉባኤ አጀንዳ በተመለከተ ሲያብራሩ ደግሞ “ማረቆ ትላንት በተወሰነው ውሳኔ ላይ የተለየ አቋም አለው። ይህንን አቋሙን በራሱ እንደ ብሔረሰብ ገልጾ፤ ሌሎች በጋራ ለመደራጀት በወሰኑት ውሳኔ ማረቆ ራሱን እንደሚያካትት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ለመግለጽ ነው” ብለዋል።

“የማረቆ ወረዳ ቀድሞም ቢሆን ከጉራጌ ጋር አብሮ፤ የጉራጌ ዞን ክልል እንዲሆን አልጠየቀም” የሚሉት የወረዳው ምክር ቤት አባል፤ የወረዳው ፍላጎት “መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በጋራ ክልል መስርቶ በልዩ ወረዳ ተደራጅቶ ለመቀጠል ነው” ሲሉ ማረቆ በአዲሱ ክልል ወደ “ልዩ ወረዳነት” የማደግ ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
የደቡብ ክልል ለሁለት ሲከፈል ይመሰረታሉ ከተባሉ ክልሎች ውስጥ አንደኛው ማረቆን ጨምሮ በጉራጌ ዞን ስር ያሉ ሁሉም ብሔረሰቦች፤ ሀድያ፣ ስልጤ፣ ሀላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳን በ“ክላስተር” አደረጃጀት የሚያሰባስብ ነው። በደቡብ ክልል ካሉ 11 ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ባለመቀበል ውድቅ ያደረገው የጉራጌ ዞን ብቻ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)