በእስር ላይ በሚገኙት በባይቶና ፓርቲ አመራር ጉዳይ፤ የፌደራል እና አዲስ አበባ ፖሊስ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ታዘዙ

በሃሚድ አወል

የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ክብሮም በርኸ ዋስትና ከተፈቀደላቸው በኋላ እስካሁን ከእስር ያልተፈቱበትን ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ታዘዙ። ትዕዛዙን የሰጠው ትላንት አርብ ነሐሴ 6፤ 2014 የተሰየመው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ልዩ ልዩ ችሎት ነው።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚው ባይቶና አመራር የሆኑት አቶ ክብሮም በርኸ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአንድ ወር ገደማ በፊት ሐምሌ 3፤ 2014 ነበር። አቶ ክብሮም ከመያዛቸው አስቀድሞ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ባለቤታቸው ነበሩ።

የክብሮም ቤተሰቦች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ የባይቶናው አመራር በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት በአቃቂ ቃሊቲ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የታሰሩትን ባለቤታቸውን ለማየት በሄዱበት ወቅት ነው። አቶ ክብሮም በፖሊስ ከተያዙ በኋላ ባለቤታቸው ከእስር መለቀቃቸውንም ቤተሰቦቻችው ጨምረው ገልጸዋል።

የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ከሁለት ቀናት በኋላ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በ2,000 ብር ዋስትና እንዲፈቱ ወስኖላቸው ነበር። የፖለቲከኛው ቤተሰቦች ለዋስትና የተጠየቀውን ገንዘብ ቢከፍሉም፤ ክብሮም ከእስር ሳይለቀቁ መቅረታቸውን አስረድተዋል። 

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ አቶ ክብሮም ለአንድ ሳምንት ገደማ ታስረው ከቆዩበት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት፤ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መዘዋወራቸውን ቤተሰቦቹ መረጃ ቢደርሳቸውም እስካሁንም ድረስ በአካል ሊያገኟቸው አለመቻላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የአቶ ክብሮም ቤተሰቦች ተጠርጣሪው ያሉበትን እንዲያሳውቋቸው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ማግኘት ባለመቻላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል። 

የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ወንድወሰን በፍቃዱ፤ የባይቶናው አመራር ከእስር እንዲለቀቁ የጠየቁበትን “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) አቤቱታ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ልዩ ልዩ ችሎት ያቀረቡት ባለፈው ወር ሐምሌ 12፤ 2014 ነበር። አቤቱታው የቀረበለት ፍርድ ቤት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “ተጠርጣሪውን በአካል ችሎት ፊት ይዘው በማቅረብ፤ አቶ ክብሮም ያልተፈቱበትን ምክንያት እንዲያስረዳ” ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይህንኑን ትዕዛዝ ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ ለሶስት ጊዜ ያህል ቢያስተላልፍም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለችሎቱ በጽሁፍ ምላሽ የሰጠው ግን ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 2፤ 2014 ነበር። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዚሁ ምላሹ፤ ተጠርጣሪውን “ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ መላኩን” ገልጿል። ይህንኑ የኮሚሽኑን ምላሽ ተከትሎ፤ የልዩ ልዩ ችሎቱ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊዎች ጉዳዩን በፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ባለፈው ረቡዕ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት በትላንትናው ዕለት ችሎት ፊት የቀረቡት የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወካይ፤ ተጠርጣሪውን “እኛ አልተረከብንም” ብለዋል። የተወካዩን ምላሽ ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ ልዩ ልዩ ችሎት፤ የሁለቱ የጸጥታ ተቋማት የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊዎች በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 10፤ 2014 ችሎት ፊት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)