በጉራጌ ዞን የሚገኙ አራት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር፤ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን በየምክር ቤቶቻቸው አጸደቁ

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የሚገኙ አራት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 7፤ 2014 በየምክር ቤቶቻቸው ባካሄዱት አስቸኳይ ጉባኤ አጸደቁ። የመስቃን እና የምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እንዲሁም የቡታጅራ ከተማ ማዕከሉን ቡታጅራ ያደረገ አዲስ ዞን ለመመስረት በተጨማሪነት የወሰኑ ሲሆን፤ የማረቆ እና ቀቤና ወረዳዎች ደግሞ ወደ ልዩ ወረዳነት ለማደግ ውሳኔ አሳልፈዋል።

የማረቆ፣ ቀቤና፣ የመስቃን፣ የምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እንዲሁም የቡታጅራ ከተማ ምክር ቤቶች፤ በ“ክላስተር” የሚደራጀውን አዲስ ክልል የመቀላቀል ውሳኔን ያጸደቁት በሙሉ ድምጽ መሆኑን የየምክር ቤቶቹ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይር” ተናግረዋል። የ“ምስራቅ ጉራጌ ዞን” የሚል ስያሜ ያለው አዲስ ዞን ለመመስረት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብም በተመሳሳይ በሙሉ ድምጽ መጽደቁን አባላቱ ገልጸዋል። 

የጉራጌ ዞን በ16 ወረዳዎች እና በስምንት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ነው። ዛሬ ውሳኔዎቻቸውን በየምክር ቤቶቻቸው ያሳለፉት የአራት ወረዳዎች እና የቡታጅራ ከተማ ምክር ቤቶች፤ ጥያቄዎቻቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገባሉ ተብሏል። “ወረዳዎች እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች የማሳለፍ ስልጣን አላቸው ወይ?” በሚል ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ፤ ምክር ቤቶቹ “ስለ ህዝብ ጥያቄ የመወያየት፤ ተወያይተውም ውሳኔ የማሳለፍ ስልጣን አላቸው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶቹ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ያጸደቁት፤ በጉራጌ ዞን ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ከተደረገ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው። የጉራጌ ዞኑ ምክር ቤት ከሌሎች አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ያደረገው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ነው።

በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበውን የ“ክላስተር” አደረጃጀት 52 የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባላት ሲቃወሙት፤ 40 ያህሉ ደግፈውታል። በዞኑ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የድጋፍ ድምጻቸውን ከሰጡ አባላት መካከል፤ የማረቆ፣ ቀቤና እና መስቃን  ወረዳ ተወካዮች ይገኙበታል ተብሏል።

በዛሬው ዕለት አስቸኳይ ጉባኤዎችን ያካሄዱት በሶስቱ ወረዳዎች ምክር ቤት ተመሳሳይ የድምጽ አሰጣጥ አካሄድ መንጸባረቁን የጉባኤው ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በጉራጌ ዞን ምክር ቤት ተወካይ የሌለው የምስራቅ መስቃን ወረዳም፤ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በሙሉ ድምጽ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ማጽደቁ ተገልጿል።  

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የምስራቅ መስቃን ወረዳ ምክር ቤት አባል፤ ምክር ቤቱ “መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተቀብሏል። ህዝቡም፤ ምክር ቤቱም ይሔን አጽድቋል” ሲሉ የወረዳ ምክር ቤቱን ውሳኔ አስረድተዋል። የወረዳ ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባኤው፤ “ምስራቅ ጉራጌ ዞን” የሚል ከነባሩ የጉራጌ ዞን የተነጠለ አዲስ ዞን ለመመስረት የቀረበ የውሳኔ ሀሳብን በሙሉ ድምጽ ማጽደቁንም አባሉ አክለዋል።

በዚህ የውሳኔ ሃሳብ፤ ለምስራቅ ጉራጌ ዞን ማዕከልነት የታጨው የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ነው። የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ይህንኑ የአዲስ ዞን መዋቅር ማጽደቁን አቶ ነጋሽ በላይነህ የተባሉ የቡታጅራ ከተማ ምክር ቤት አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም የ“ክላስተር” አደረጃጀትን በመደገፍ ድምጽ መስጠቱንም አመልክተዋል። 

በ“ክላስተር” የመደራጀቱ እና አዲስ ዞን የመመስረቱ ሃሳብ “የከረመ ጥያቄ ነው” ይላሉ አቶ ነጋሽ። የቡታጅራ ከተማ ካለበት “ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ” ባሻገር፤ “የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የዞኑ መንግስት ቸልተኝነት፣ በቂ ውክልና አለማግኘት እና ኃላፊነትና ጥቅምን እኩል አለመጋራት” ጥያቄው እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑንም አብራርተዋል።

የአዲሱን ዞን ምስረታ በተመለከተ በመስቃን ወረዳ ምክር ቤትም በዛሬው ዕለት ተመሳሳይ ውሳኔ መተላለፉን የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል። አቶ መሐመድ ሀሰን የተባሉ የወረዳው ምክር ቤት አባል ዛሬ ስለተላለፈው ውሳኔ ሲያስረዱ፤ “ምስራቅ ጉራጌ ዞን የተባለ መስርተን፤ አዲስ በሚደራጀው ክልል ውስጥ እንድንካተት የሚል ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ምክር ቤቱ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን በተመለከተ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁንም አክለዋል።

በጉራጌ ዞን ስር ያሉት ሁለት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር አዲስ ዞን ለመመስረት በዛሬው ጉባኤዎቻቸው እንደወሰኑት ሁሉ፤ ሌሎች ሁለት ወረዳዎች ደግሞ ወደ “ልዩ ወረዳነት” አድገው አዲሱን ክልል ለመቀላቀል ውሳኔ አሳልፈዋል። ወደ ልዩ ወረዳነት የማደግ ጥያቄን በምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁት የቀቤና እና ማረቆ ወረዳዎች ናቸው።

የቀቤና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብደላ የዛሬውን ውሳኔ ሲያብራሩ፤ “ከዚህ በፊት የልዩ ወረዳነት ጥያቄ አቅርበናል። አሁንም ልዩ ወረዳችንን መንግስት አጽድቆልን፤ ልዩ ወረዳችንን ይዘን ከአዲሱ ክልል ጋር መቀላቀል አለብን ብለን ነው ያጸደቅነው” ብለዋል። አቶ አብደላ “መንግስት እና ፓርቲ ያስቀመጠው አቅጣጫ” ሲሉ የጠሩትን የ“ክላስተር አደረጃጀት”፤ የቀቤና ወረዳ ምክር ቤት “በሙሉ ድምጽ” ማጽደቁንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

እንደ ቀቤና ወረዳ ሁሉ የማረቆ ወረዳ ምክር ቤትም በልዩ ወረዳነት ተደራጅቶ አዲሱን ክልል ለመቀላቀል መወሰኑን አንድ የምክር ቤት አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የአራቱ የጉራጌ ዞን ወረዳዎች እና የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች፤ በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤዎቻቸው ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች በቀጥታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚያስገቡ አባላቱ ጠቁመዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ተረፈ በበኩላቸው፤ ጥያቄው የሚቀርበው በዞን እና በክልል ምክር ቤቶች አልፎ መሆኑን አስረድተዋል። “ጥያቄው በየደረጃው ያለውን የመንግስት እርከን ጨርሶ መምጣት አለበት” የሚሉት አቶ ተረፈ “ጥያቄያቸውን አቅርበው በሁለት ዓመት መልስ ካላገኙ፤ በቀጥታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማቅረብ መብት አላቸው” ሲሉ ሂደቱን አብራርተዋል። 

አቶ ተረፈ ይህን ቢሉም የቡታጅራ ከተማ ምክር ቤት አባሉ አቶ ነጋሽ ግን መጀመሪያ ጥያቄ ሊቀርብለት ይገባል በተባለው የጉራጌ ዞን ላይ “እምነት የለንም” ባይ ናቸው። “ለየትኛው ዞን እናቀርባለን? ስለዚህ በዚህ ምክንያት እሱን ዘልለን ወደሚመለከተው አካል ጥያቄያችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ እናደርሳለን” ሲሉ መሰል ጥያቄዎች የሚቀርቡበትን ሂደት እና የጊዜ ቆይታ እንደማይጠብቁ ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪን፣ የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤን፣ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊን እንዲሁም የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። በተመሳሳይ ለደቡብ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ተመሳሳይ ጥያቄ ብናቀርብም “ጉዞ ላይ ነኝ” በማለታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)