የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ በደቡብ ክልል አደረጃጀት ጉዳይ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው

በሃሚድ አወል

መደበኛው ጉባኤውን ከአንድ ወር በፊት ያደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ በደቡብ ክልል አደረጃጀት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው። ሁለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 11፤ 2014 ለሚደረገው ለዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ እንደተደረገላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ፤ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባውን በመጪው ረቡዕ እንደሚያካሂድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። አቶ ተረፈ ምክር ቤቱ “ከደቡብ ክልል ጋር ተያይዞ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ይኖራሉ” ሲሉ ስብሰባው የተጠራበትን ምክንያት ገልጸዋል።

ፎቶ፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

በደቡብ ክልል የሚገኙ አስር ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች፤ በሁለት የተለያዩ ክልሎች የመደራጀት ጥያቄያቸውን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 28፤ 2014 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት አስገብተዋል። ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች መካከል የመጀመሪያውን ክልል ለመመስረት በየምክር ቤቶቻቸው የወሰኑት ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ናቸው።

እነዚህ በደቡብ ክልል ስር ያሉ መዋቅሮች ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት ባደረጓቸው የምክር ቤት ጉባኤዎቻቸው በሌላ ሁለተኛ ክልል ለመደራጀት ውሳኔ ያሳለፉት ደግሞ የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ስልጤ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ናቸው።    

የዞኖችን እና ልዩ ወረዳዎችን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት፤ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ክፍሌ ዋና ናቸው። ጥያቄዎቹን የያዙ ሰነዶች ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ “የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥያቄው ላይ ውይይት አካሄዶ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ወስኖ የሚያሳውቅ ይሆናል” ብለው ነበር።

ፎቶ፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አቶ አገኘሁ በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ “ባለኝ መረጃ መሰረት ወይይት እያደረገ ያለ አንድ ዞን ብቻ ነው። የአንድ ዞን መረጃ እንደደረሰ ወደ ተግባር የምንገባ ይሆናል” ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጉራጌ ዞንን ውሳኔ እንደሚጠባበቅ ጠቁመው ነበር። አፈ ጉባኤው ከዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ጥያቄውን በተቀበሉ ማግስትም በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው “የጉራጌ ዞን ጥያቄ እየተጠበቀ ነው። በቅርቡ ያቀርባል ተብሎ ይታሰባል” ቢሉም የዞኑ ምክር ቤት ግን ከሌሎች ዞኖች የተለየ ውሳኔ ወስኗል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ከሶስት ቀናት በፊት ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ጉባኤ፤ ከሌሎች አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር በ“ክላስተር” እንዲደራጅ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብን በአብላጫ ድምጽ ውድቅ አድርጎታል። በዞን ምክር ቤት ስብሰባው ላይ ከተገኙ 92 አባላት መካካል 52ቱ የ“ክላስተር” አደረጃጃትን ሲቃወሙ፤ ቀሪ 40 አባላት ደግሞ የድጋፍ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ከጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔ ሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በዞኑ የሚገኙ አራት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አስቸኳይ ጉባኤዎች አካሄደው የ“ክላስተር” አደረጃጀትን በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል። የ“ክላስተር” አደረጃጃትን ያጸደቁት የማረቆ፣ ቀቤና፣ መስቃን እና ምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እንዲሁም የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ናቸው።

የመስቃን እና ምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እንዲሁም የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር፤ ማዕከሉን ቡታጅራ ያደረገ አዲስ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ለመመስረት በየምክር ቤቶቻቸው ሲወስኑ፤ የማረቆ እና ቀቤና ወረዳዎች ደግሞ ወደ ልዩ ወረዳነት ለማደግ ውሳኔ አሳልፈዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሁለት አዲስ ክልሎች ምስረታ ጥያቄን በተቀበሉት ስነ ስርዓት ላይ፤ የዞን እና ልዩ ወረዳ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት “ይደራጃሉ የተባሉት ክልሎች ጥያቄ ሲፈታ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

አቶ አገኘሁ የመዋቅር ጥያቄዎች የሚፈቱበትን ሂደት ሲያብራሩም “ይሄ ሲፈታ በቀጥታ የልዩ ወረዳ፣ የዞን የመሳሰሉት የመዋቅር ጥያቄዎች አብረው ምላሽ የሚገኙበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለው ነበር። አፈጉባኤው ከብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ ለክልል ጥያቄ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ሌሎች የሚከናወኑ ሂደቶች እንዳሉ አስታውቀዋል። “ይሄንን የሚያደራጁ የሚከታተሉ ኮሚቴዎች፤ ህዝበ ውሳኔም ከሆነ ህዝበ ውሳኔ የሚሰጥበት ስርዓት ሌሎች ነገሮች ይመቻቻሉ ማለት ነው” ሲሉ ከምክር ቤቱ ውሳኔ በኋላ የሚኖረውን ሂደት አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)