የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ከ“ክላስተር” አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ያሳለፈውን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አስገባ

– የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ በዞኑ ያሉ ስድስት የወረዳ እና ሁለት የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ውሳኔዎችንም ተቀብሏል

በሃሚድ አወል

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ውድቅ ያደረገበትን የምክር ቤት ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 9፤ 2014 አስገባ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን የሚደግፍ ውሳኔ በየምክር ቤቶቻቸው ያሳለፉ ስድስት የወረዳ እና ሁለት የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶችን ውሳኔንም በዛሬው ዕለት ተቀብሏል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ፤ “ክላስተርን የሚደግፉ እና የሚቃወሙ አካላት” ጥያቄያቸውን ለምክር ቤቱ ማቅረባቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገባው ውሳኔ፤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀውን ነው። 

የዞኑ ምክር ቤት በዚሁ አስቸኳይ ጉባኤው፤ የጉራጌ ዞን በአጎራባች ከሚገኙ ሌሎች መዋቅሮች ጋር በ“ክላስተር” ለማደራጀት የቀረበውን ምክረ ሀሳብ በ52 ተቃውሞ እና በ40 ድጋፍ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አርሽያ አህመድ ከሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮች ጋር በመሆን ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ፤ “የእዚህን ጉባኤ ውሳኔ ይዘን ነው የመጣነው። ፈርመው ተቀብለውናል። [ሆኖም] በአካል አግኝተናቸው አጠቃላይ ማብራሪያ የሰጠንበት ሁኔታ የለም” ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አመራሮችን ማነጋገር አለመቻላቸውን ተናግረዋል። 

ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በገባው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የውሳኔ ሰነድ ላይ፤ በሐሙሱ አስቸኳይ ጉባኤ የተሳተፉ አባላት ስም ዝርዝር እና ቃለ ጉባኤ በአባሪነት ተያይዟል። ይህ የውሳኔ ሰነድ፤ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት እና ለክልሉ ርዕስ መስተዳድርም ግልባጭ ተደርጓል።  

ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ለሰጡት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አመራሮች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ “በዞኑ የሚገኙ ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ደግፈው በየምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ ማሳለፋቸው እንዴት ታዩታላችሁ?” የሚለው ይገኝበታል። አፈ ጉባኤ አርሽያ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አስቸኳይ ጉባኤው የተካሄደው “የሁሉም አካባቢ ተወካይ በተገኘበት” እና በ“አጀንዳ ተይዞ” መሆኑን ገልጸዋል። 

“እኔ ከዚያ ውጭ እየተካሄዱ ያሉ ጉባኤዎች ላይ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ። የሚመለከተው አካል አለ። ራሱ ከህግ አንጻር ሄዶበት፤ እየሆኑ ያሉ ጉባኤዎች ላይ መልስ መስጠት ይችላል” ሲሉ ለጉዳዩ ምላሽ መስጠት ያለበት ሌላ የመንግስት አካል መሆኑን ጠቁመዋል። ከትላንት በስቲያ እና በትላትናው ዕለት በተካሄዱ የስድስት ወረዳዎች እና የሁለት ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤዎች ያጸደቋቸው የአዲስ ዞን ምስረታ እና ወደ ልዩ ወረዳ የማደግ ውሳኔዎችም እንዲሁ ጥያቄ ቀርቦባቸዋል።  

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እነዚህን የመዋቅር ጥያቄዎች በተመለከተ “የጉራጌ ዞን የሚያውቀው ነገር አለ ወይ?” የሚል ጥያቄ ለዞኑ ምክር ቤት አመራሮች አቅርባለች። ሄሪያ ወርቁ የተባሉ የዞኑ ምክር ቤት አመራር “ለዞን ምክር ቤት ምንም አይነት መረጃ የቀረበበት ሁኔታ ስለሌለ፤ ከእነርሱ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በሚዲያ የምንገልጸው ምንም አይነት ነገር አይኖርም” ሲሉ መልሰዋል። 

በጉራጌ ዞን ምክር ቤት መግለጫ ላይ ጉዳያቸው የተነሳው ስድስት ወረዳዎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች፤ በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቋቸውን ውሳኔዎች ዛሬ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አስገብተዋል። ውሳኔያቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ካስገቡት ውስጥ የቡኢ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ይገኝበታል። የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት በአፈ ጉባኤው አማካኝነት ውሳኔውን  ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባቱን የቡኢ ከተማ ከንቲባ አቶ ይሽልጌታ በላይነህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

በተመሳሳይ የቀቤና፣ ማረቆ፣ መስቃን፣ ምስራቅ መስቃን፣ ሶዶ እና ደቡብ ሰዶ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች ውሳኔዎቻቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቡታጅራ ከተማ አስተዳደርም በምክር ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን የከተማው ከንቲባ ናስር ጀማል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል።  

የቀቤና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብደላ ጀማል፤ የወረዳው ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ጭምር አስገብተናል ብለዋል። ይህንኑ ውሳኔ ለጉራጌ ዞን በደብዳቤ እንደሚያሳውቁም ጠቁመዋል። የወረዳው ምክር ቤት ውሳኔ በቀጥታ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲገባ የተደረገው፤ ያለው “ጊዜ አጭር በመሆኑ ነው” ይላሉ። “የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዚህ ሳምንት ጉባኤ ጠርቷል። የጉባኤው ቀን አጭር ስለሆነ፤ እነሱም በቶሎ አይተው ፈትሸው ለውሳኔ ለማቅረብ ጊዜ ስለሌላቸው፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀጥታ ይዘን መጥተናል” ሲሉ አቶ አብደላ ምክንያታቸውን አብራርተዋል። 

የመስቃን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀሰን ከድር ግን ውሳኔው በቀጥታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲገባ የተደረገው በሌላ ምክንያት ነው ባይ ናቸው። “ለዞን ብናስገባ ይሄ ተፈጻሚ አይሆንም። እንደ አንድ ምክር ቤት አባል አይተነዋል። ሊሆን ስለማይችል ስለዚህ በቀጥታ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መድረስ አለበት የሚለውን ነገር ይዘን ነው የመጣነው” ሲሉ ውሳኔው በየደረጃው ላለው የመንግስት እርከን በመጀመሪያ ያልቀረበበትን ምክያት አስረድተዋል። 

የወረዳዎቹን እና የከተማ አስተዳደሮቹ የየምክር ቤቶቻቸውን ውሳኔ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ማስገባታቸውን ያረጋገጡት የፌደሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ፤ ሁለቱም አካላት ባስገቡት ጥያቄ ላይ “ሐሙስ አቅጣጫ ሊቀመጥ ይችላል” ሲሉ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፌደሬሽን ምክር ቤት በሐሙሱ አስቸኳይ ስብሰባው፤ ዋነኛ አጀንዳው የደቡብ ክልል አደረጃጃት ጉዳይ መሆኑን አቶ ተረፈ ትላንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት መረጃ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

በድቡብ ክልል የሚገኙ 10 ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ከሁለት ሳምንት ባካሄዷቸው ጉባኤዎች፤ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበውን የ“ክላስተር” አደረጃጃት ማጽደቃቸው ይታወሳል። ይህ የ“ክላስተር” አደረጃጀት ተግባራዊ ከሆነ አሁን ያለው የደቡብ ክልል ለሁለት ይከፈላል። 

ይህን አደረጃጀት ተከትለው የመጀመሪያውን ክልል ለመመስረት የወሰኑት የወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዲዮ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የባስኬቶ፣ ደራሼ፣ አሌ፣ ቡርጂ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። የሀድያ፣ ከንባታ ጠንባሮ፣ ስልጤ እና ሀላባ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳ ሁለተኛውን ክልል የሚመስረቱ መዋቅሮች ናቸው። የጉራጌ ዞን ሁለተኛውን ክልል እንዲቀላቀል የውሳኔ ሃሳብ ቢቀርብለትም፤ በምክር ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)