የባልደራስ ፕሬዝዳንቱ እስክንድር ነጋ “የመታፈን አደጋ ደርሶባቸዋል” የሚል እምነት እንደሌለው አስታወቀ

በሃሚድ አወል

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ በቅርቡ ከፓርቲው ፕሬዝዳንትነት መልቀቃቸውን ያሳወቁት አቶ እስክንድር ነጋ “የመታፈን አደጋ ደርሶባቸዋል” የሚል እምነት እንደሌላው አስታወቀ። ፓርቲው ከዚህ በኋላ በሚከተለው የትግል አቅጣጫ የፖለቲካ አንቂነት (አክቲቪዝም) ላይ እንደማያተኩር ገልጿል።

ፓርቲ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 9፤ 2014 አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የባልደራስ ፓርቲ መግለጫ ዋና ትኩረቱን ያደረገው በቅርቡ ከፓርቲ ፕሬዝዳንትነት መልቀቃቸውን ባስታወቁት አቶ እስክንድር ጉዳይ ላይ ነው።

የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው፤ “እስክንድር ቢሮ መግባት ያቆመው ከሐምሌ 16፤ 2014 ጀምሮ ነው። ከቢሮው እና ከስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ጋር ያለው ግንኙነት [ከዚያ በኋላ] ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል” ሲሉ አቶ እስክንድር ከፓርቲው ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ይፋዊ ግንኙነት ያደረጉበትን ጊዜ ጠቁመዋል። አቶ እስክንድር በአሁኑ ወቅት ስላሉበት ሁኔታ  የፓርቲው አመራሮች ከእርሳቸው በቀጥታ መረዳት ባይችሉም፤ “የመታፈን አደጋ ደርሶባቸዋል” የሚል እምነት እንደሌላቸው ግን አቶ አምሃ አስታውቀዋል።  

የፓርቲው አመራሮች የአቶ እስክንድርን መልቀቅ ያወቁት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 5፤ 2014 ሰሜን አሜሪካ በሚገኘው የባልደራስ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ በኩል በፓርቲው የማህበራዊ ትስስር ገጽ በተላለፈ የደብዳቤ መልዕክት መሆኑን አቶ አምሃ ገልጸዋል። ለባልደራስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተጻፈው ይህ ባለ አንድ ገጽ ደብዳቤ የተጻፈበት ቀን ሐምሌ 16፤ 2014 እንደሆነ በፓርቲው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ከመልዕክቱ ጋር አብሮ የተያያዘው ፎቶ ያሳያል።

በእጅ ጹሁፍ በቀረበው በዚህ ደብዳቤ ላይ አቶ እስክንድር፤ “ተረኛው ጨቋኝ መንግስት በባልደራስም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና ሳቢያ፣ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ” በማለት አስፍረዋል። የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ በዛሬው መግለጫ ይህንኑ በማንሳት በሰጡት አስተያየት፤ “እስክንድርን ያህል የጽናት ተምሳሌት፤ ባለበት የፖለቲካ ጫና ምክንያት ከፖለቲካ ትግሉ ገሸሽ አለ ማለት፤ ፖለቲካው ላይ ያለው ተጽዕኖ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መረዳት [የሚያስችል ነው]” ሲሉ ተናግረዋል።

እርሳቸው ይህን ቢሉም በዛሬው የፓርቲው መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል “ባልደራስ እስክንድርን ከድቷል ወይስ እስክንድር ነው ባልደራስን የከዳው?” የሚለው ይገኝበታል። ለዚህ ጥያቄ ዶ/ር በቃሉ በሰጡት ምላሽ፤ “እስክንድርን ሊከዳ የሚችል ፓርቲ አይኖረንም። የተሰበሰብነውም እስክንድርን ብለን ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

ባልደራስ በዛሬው መግለጫው፤ ከፕሬዝዳንቱ መልቀቂያ የማስገባት ጉዳይ በተጨማሪ የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ የተመለከተ ማብራሪያ አቅርቧል። የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የባልደራስ የወደፊት አቅጣጫ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈቱ የሚችሉበትን የፖሊሲ አማራጮች በማመንጨት፤ ወደ ህዝብ ሰርጸው የሚገቡበትን መደላደል በማመቻቸት ላይ የሚያተኩር ይሆናል” ብለዋል።  

“በአሁኑ ጊዜ የኦህዴድ-ብልጽግና መንግስትን አፋዊ አቀራራብ ሳይሆን ተግባራዊ ክንውን፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በተለይ የአዲስ አበባ ህዝብ በሚገባ እየተገነዘበ እንደመጣ ይታመናል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ህዝብ የፖለቲካ መብቱን እና የኢኮኖሚ ጥቅሙ እየተጎዳ ስለመሆኑ የፖለቲካ አንቂ የሚፈልግ አይደለም። የኑሮ መክብድ እና የፖለቲካው መዝቀጥ በተጨባጭ አንቅቶታል” ሲሉም ባልደራስ ከዚህ በኋላ በ“ፖለቲካል አክቲቪዝም” ላይ ማተኮር ያልፈለገበትን ምክንያት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)