ባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤውን በአንድ ወር ማራዘሙን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከ12 ቀናት በኋላ ሊያካሄደው የነበረውን ጠቅላላ ጉባኤ ወደ መስከረም ወር አራዘመ። ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤውን መራዘም ይፋ ያደረገው ትላንት ሰኞ ነሐሴ 9፤ 2014 በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። 

በመግለጫው ላይ ከተገኙት የባልደራስ አመራሮች አንዱ የሆኑት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ “ነሐሴ 22 ብለን ይዘነው ነበር፤ ያልተሟሉ ነገሮች ስላሉ ከነሐሴ 22 ትንሽ እናራዝመዋለን” ሲሉ ተናግረዋል። ዶ/ር በቃሉ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ “ያልተሟሉ ነገሮች አሉ” ቢሉም ጉዳዮቹ ምን እንደሆኑ ግን አልጠቀሱም። ሆኖም ጉባኤው በመስከረም ወር እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በመጋቢት 2012 በክልላዊ ፓርቲነት የተመሰረተው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፤ ፓርቲው በየሁለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ መካሄድ እንዳለበት ይደነግጋል። ባልደራስ በመጪው ጠቅላላ ጉባኤው፤ ከክልላዊ ፓርቲነት ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት የሚሳድገውን ውሳኔ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። 

በቅርቡ ከፓርቲው ፕሬዝዳንትነት መልቀቃቸውን ባስታወቁት አቶ እስክንድር ነጋ ምትክ ፓርቲውን የሚመራ ፕሬዝዳንት  የሚመረጠውም በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ነው። የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ “ከጠቅላላ ጉባኤው በኋላ ሰፋ ያለ ሽግሽግ ይኖራል” ሲሉ ከመስከረሙ ጉባኤ በኋላ በፓርቲው ውስጥ ጉልህ ለውጦች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል። 

ባልደራስ በቅርቡ ሊያካሄድ ያቀደውን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ፤ እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለማሳወቁን ቦርዱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቆ ነበር። ስለዚሁ ጉዳይ በትላንቱ መግለጫ ላይ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን በተመለከተ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አለማስገባቱን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፤ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የሚያካሄድ ከሆነ የቦርዱ ተወካይ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ከ30 ቀናት በፊት አስቀድሞ ማሳወቅ እንዳለበት ይደነግጋል። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በአዋጁ እና በፓርቲው መተዳሪያ ደንብ መሰረት የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ከሚገባው ጊዜ በሶስት ወር የዘገየ እንደሆነ እና ቦርዱ በሚያስቀምጠው የጊዜ ገደብ ጉባኤውን ሳያካሄድ ከቀረ ከምዝገባ እንደሚሰረዝ በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)