በሃሚድ አወል
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2015 በጀት ዓመት፤ በስምንት ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ እና በንግድ ስራ ከተሰማሩ የሃይማኖት ተቋማት ግብር እና ታክስ መሰብሰብ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። ቢሮው ታክሱን የሚሰበስበው በሆቴል ንግድ እና በህንጻ ኪራይ ላይ ከተሰማሩ የሃይማኖት ተቋማት ነው።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ውሳኔውን ያሳወቀው፤ ለስምንት “ሪጂኦፖሊታን” የከተማ አስተዳደር የገቢዎች መስሪያ ቤቶች ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ነሐሴ 11፤ 2014 በላከው ደብዳቤ ነው። የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጸጋ ጥበቡ፤ ውሳኔው ማዕከል ያደረገው “ከአምልኮተ ስርዓት ማስፈጸሚያ ሽያጭ ጋር ያልተያያዙትን እና እንደማንኛውም ነጋዴ TIN number አውጥተው የሚሰሩትን የሃይማኖት ተቋማት” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የፌደራል የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅም ሆነ የአማራ ክልል የገቢ ግብር አዋጅ፤ የሃይማኖት ተቋማት በሚሰጡት የእምነት አገልግሎት ወይም ከአምልኮት ጋር የተገናኙ አገልግሎቶቻቸው ከታክስ ነጻ መሆናቸውን ደንግገዋል። ሆኖም የሃይማኖት ተቋማት፤ ከተቋቋሙበት ዓላማ ጋር በማይገናኝ የንግድ ስራ ተሰማርተው የሚያገኙት ገቢ ከግብር ነጻ አለመሆኑ በ2008 ዓ.ም በወጣው የአማራ ክልል የገቢ ግብር አዋጅ ላይ ሰፍሯል።
ከስድስት ዓመት በፊት የወጣው የክልሉ የገቢ ግብር አዋጅ ይህን ቢደነግግም፤ አፈጻጸሙ ግን “በተንጠባጠበ መልክ፤ በየአካባቢው ባሉ የገቢዎች ተቋም አመራር እና ባለሙያዎች የሚተገበር እንደነበር” ዶ/ር ጸጋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የአሁኑ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ውሳኔ፤ ይህን “የተንጠባጠበ አፈጻጸም” አንድ አይነት መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ያቀደ መሆኑንም የቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል።
በእርሳቸው ተፈርሞ ለስምንት የከተማ አስተዳደሮች ከትላንት በስቲያ የተላከው ደብዳቤ፤ የሃይማኖት ተቋማት “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ” በሆቴል ንግድ ስራ ዘርፍ እና በህንጻ ኪራይ ተሰማርተው ገቢ የሚያገኙ ከሆነ፤ ለከተሞቹ ግብር የማስከፈል ስልጣን ይሰጣቸዋል። ይህ ስልጣን በደብዳቤው የተሰጣቸው “ሪጂኢፖሊታን” ከተሞች፤ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ወልዲያ እና ደብረ ታቦር ናቸው።
ዶ/ር ጸጋ ስምንቱ ከተሞች ስለተመረጡበት መስፈርት ሲያብራሩ፤ “የሃይማኖት ተቋማቱ ህንጻ ቢያከራዩም፣ በሆቴል ላይ ቢሰሩም ደህና ገቢ ሊያገኙባቸው የሚችሉ ትላልቅ ከተሞች ናቸው። በእነዚህ ትላልቅ ከተሞች እንጀምር እና ከዚያ በኋላ እያሰፋን እንሄዳለን። ሁሉም ቦታ በአንዴ መጀመር አግባብ አይደለም” ብለዋል። ከሃይማኖት ተቋማት ግብር ለመሰብሰብ ሲሞከር “ ‘እንዴት እንከፍላለን?’ የሚሉ ነገሮች ሊነሱ እንደሚችሉ እንጠብቃለን” የሚሉት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ፤ ይህን ተቃውሞ ለማስቀረት “የማስረዳት ስራ እንሰራለን” ሲሉ አክለዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ከተቋማቱ የሚሰበስበን ግብር በቅጡ ለማወቅ፤ በተመረጡት ከተሞች ህንጻዎችን አከራይተው እና በሆቴል ንግድ ተሰማርተው የሚገኙ ተቋማትን መረጃ ማሰባሰብ መጀመሩን ዶ/ር ጸጋ ገልጸዋል። “ምን ያህል ገንዘብ ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዛችኋል?” በሚል ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “አቅማቸውን ስናውቅ ነው potentially ምን ያህል ልንሰበስብ እንደምንችል የምናውቀው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)