ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ፤ ተሰናባቹ አቶ ላቀ አያሌውን ተክተው የገቢዎች ሚኒስቴርን እንዲመሩ ተሾሙ

በተስፋለም ወልደየስ

በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሆነው በመስራት ላይ የነበሩት አይናለም ንጉሴ፤ የገቢዎች ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት እንዲመሩ ተሾሙ። ወይዘሮ አይናለም በቦታው የተሾሙት፤ ላለፈው ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት መስሪያ ቤቱን በሚኒስትርነት ሲመሩ የቆዩትን አቶ ላቀ አያሌውን በመተካት ነው። 

አቶ ላቀ የሚኒስትርነት ኃላፊነታቸውን የለቀቁት፤ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ውጭ ሀገር ስለሚጓዙ ነው ተብሏል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ አባል የሆኑት አቶ ላቀ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት ካካሄደው ስብሰባ በኋላ የአሸኛኘት ስነ ስርዓት ተደርጎላቸው ነበር።፡

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ለተሰናባቹ ሚኒስትር በተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 14፤ 2014 የሽኝት ፕሮግራም በመስሪያ ቤታቸው ተካሄዶላቸዋል። በዚሁ የሽኝት መርሃ ግብር ከአዲሲቷ ሚኒስትር ጋር በይፋ የስራ ርክክብ ያደረጉት አቶ ላቀ፤ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ለመንግስት ጥያቄ ያቀረቡት ከሰባት ወራት በፊት መሆኑን መናገራቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል። 

አቶ ላቀ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት በሒሳብ መዝገብ አያያዝ (አካውንቲንግ) ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩት ደግሞ በቢዝነስ አስተዳደር (ማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድምኒስትሬሽን) ነው። በአማራ ክልል ከወረዳ እስከ ዞን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት አቶ ላቀ አያሌው፤ ከጥቅምት 2011 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከአምስት ወራት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ሰርተዋል። 

ፎቶ፦ የገቢዎች ሚኒስቴር

የእርሳቸውን የሚኒስትርነት ቦታ የተኩት ወ/ሮ አይናለም ንጉሴም፤ በአማራ ክልል በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ በማገልገል ላይ የነበሩ ናቸው። አዲሷ ተሿሚ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በአማራ ክልል የኢኮኖሚ ጉዳዮች ክላስተርን የማስተባበር ኃላፊነትን ተረክበው ሲሰሩ የቆዩ ናቸው። ወ/ሮ አይናለም ይህ የኃላፊነት ቦታ የተሰጣቸው በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ ነበር።  

የገቢዎች ሚኒስቴርን ለመምራት አስረኛ ተሿሚ መሆናቸው የተነገረላቸው ወ/ሮ አይናለም፤ ለፌደራል መስሪያ ቤት ሹመትም እንግዳ አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በመስከረም 2011 የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን በአዲስ መልክ ሲያዋቅሩ ከተሾሙ 55 ሚኒስትር ዲኤታዎች አንዷ እርሳቸው ነበሩ። ይህን ሹመት ተከትሎም ወ/ሮ አይናለም በግብርና ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታነት ለሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ሰርተዋል። 

ፎቶ፦ የግብርና ሚኒስቴር

ወ/ሮ አይናለም የመንግስት ተሿሚ ከመሆናቸው አስቀድሞ ረጅም ጊዜያቸውን ያሳለፉት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ነው። አዲሲቷ ሚኒስትር፤ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ባገኙበት የወሎ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ለሁለት ዓመት አገልግለዋል። በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ወ/ሮ አይናለም፤ ባለፈው ዓመት ሰኔ በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የገዢው ብልጽግና ፓርቲን በመወከል በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ምርጫ ክልል ለፓርላማ ተወዳድረው አሸንፈዋል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)