የአማራ ክልል መንግስት የምዕራብ ጎጃም ዞንን ለሁለት የሚከፍለውን ውሳኔ ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

በሃሚድ አወል

በአማራ ክልል ስር የሚገኘው የምዕራብ ጎጃም ዞንን ለሁለት ለመክፈል የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጀመራቸው ተገለጸ። ውሳኔው ተግባራዊ ሲደረግ በምዕራብ ጎጃም ዞን ስር የሚገኙ ሰባት ወረዳዎች እና ሶስት የከተማ አስተዳደሮች ራሱን የቻለ አዲስ ዞን ይመሰርታሉ። 

የምዕራብ ጎጃም ዞን በአሁኑ አወቃቀሩ 14 ወረዳዎች እና ስምንት የከተማ አስተዳደሮችን በስሩ ያቀፈ ነው። 1.2 ሚሊዮን ሄክታር የሚሸፍን የቆዳ ስፋት ባለው በዚህ ዞን ስር ከሚተዳደሩ ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የተወሰኑት፤ “የአገልግሎት እና የልማት ተደራሽነት ችግርን” በማንሳት “የዞን ይከፈልልን” ጥያቄ ለዓመታት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

“አስር ዓመት ገደማ ያስቆጠረ ነው” የተባለውን ይህን ጥያቄ፤ ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው ላይ የተመለከተው የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የዞን መከፈሉን ጥያቄ ተቀብሎ ውሳኔ አሳልፏል። ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው፤ ጉዳዩን እንዲያጠና የተዋቀረው የቴክኒክ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ከመረመረ በኋላ መሆኑ ተገልጿል። 

የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ የምዕራብ ጎጃም ዞን ለሁለት እንዲከፈል የተደረገው “ከስፋቱም አንጻር ትልቅ ዞን ስለሆነ እና ብዙ ህዝብ ስለሚኖርበት” እንደሆነ ተናግረዋል | ፎቶ፦ ከዋልታ ቲቪ የተወሰደ

የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ የምዕራብ ጎጃም ዞን ለሁለት እንዲከፈል የተደረገው “ከስፋቱም አንጻር ትልቅ ዞን ስለሆነ እና ብዙ ህዝብ ስለሚኖርበት” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “የዞን ይከፈልልን” ጥያቄ ሲያቀርቡ የቆዩት የምዕራብ ጎጃም ዞን ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች፤ በባህር ዳር ከተማ አቅራቢያ የሚገኙ መሆናቸውን አቶ ግዛቸው ጠቅሰዋል።

የእነዚህ አካባቢዎች ነዋሪዎች የዞን አገልግሎቶችን ለማግኘት የምዕራብ ጎጃም ዞን ማዕከል ወደሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ ረዥም ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር የሚሉት የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፤ በዞኑ የሚኖረው ማህበረሰብ “ያለ በቂ ምክንያት በጣም እየተቸገረ እንደሆነ ጥያቄ ሲያነሳ ነበር” ሲሉ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ችግር ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት የክልሉ መንግስት በወረዳዎቹ እና የከተማ አስተዳደሮቹ ጥያቄውን ተገቢነት አምኖበት ውሳኔውን እንዳሳለፈ አብራርተዋል።

ይህንኑ የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ውሳኔ፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ከአስር ቀናት ገደማ በፊት በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል። ራሱን ችሎ የሚደራጀው አዲሱ ዞን “በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ የሚገባው” ከአንድ ዓመት በኋላ በ2016 ዓ.ም. እንደሚሆን በደብዳቤያቸው ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለሁለት የሚከፈለው የምዕራብ ጎጃም ዞን መጪውን 2015 ዓመት በ“መዘጋጃ ጊዜነት” እንዲጠቀም አሳስበዋል።

“የዞን ይከፈልልን” ጥያቄ ሲያቀርቡ በነበሩ መዋቅሮች ስር ያሉ ነዋሪዎች፤ የዞን አገልግሎቶችን ለማግኘት የምዕራብ ጎጃም ዞን ማዕከል ወደሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ ረዥም ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር | ፎቶ፦ ከይሁኔ በላይ ዩቲዩብ ቪዲዮ የተወሰደ

የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የዝግጅት ጊዜ ያስፈለገው “በአንድ ጊዜ ሁሉን ነገር አሟልቶ ወደ ስራ መግባት ስለማይቻል” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ከፍተኛ በጀት ያስፈልጋል” የሚሉት አቶ ግዛቸው፤ የዞን መከፈል ውሳኔው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት “ተጨማሪ የሰው ኃይል መቅጠር” እና “ቢሮዎች መገንባት” እንደሚያሻም አስረድተዋል።

ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ነሐሴ 5፤ 2014 በጻፉት ደብዳቤ “የሚከፈለው ዞን አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ተጨማሪ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስችል ስራ መሰራት አለበት” ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀው ነበር። ይህንን የርዕስ መስተዳድሩን ማሳሰቢያ ተከትሎ የምዕራብ ጎጃም ዞን ቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጀመሩን የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመኑ ታደለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከቅድመ ዝግጅት ስራዎቹ መካከል የዞን አደረጃጃትን በተመለከተ ውይይቶች ማድረግ አንዱ መሆኑን የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጠቁመዋል። “የዞን ይከፈልልን ጥያቄን በኮሚቴነት ሲያስተባብሩ የነበሩ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይቶች ተጀምረዋል” የሚሉት አቶ ዘመኑ፤ በምዕራብ ጎጃም ዞኑ ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ደግሞ በዚህ ሳምንት ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል። 

ከምዕራብ ጎጃም ዞን ተለይተው የራሳቸውን ዞን ለማደራጀት ጥያቄ ካቀረቡት መዋቅሮች ውስጥ አንዱ የመርዓዊ ከተማ አስተዳደር ነው | ፎቶ፦ የመርዓዊ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን

ከምዕራብ ጎጃም ዞን ተለይተው የራሳቸውን ዞን ለማደራጀት ጥያቄ ካቀረቡት መዋቅሮች ውስጥ ሶስቱ የከተማ አስተዳደሮች ሲሆኑ እነርሱም ዱርቤቴ፣ መርዓዊ እና አዴት ናቸው። አዲሱን ዞን ከሚቀላቀሉት ሰባት ወረዳዎች ውስጥ አምስቱ የሚገኙት  በባህር ዳር አቅራቢያ ነው። የአማራ ክልል መንግስት መቀመጫ ለሆነችው ባህር ዳር የሚቀርቡት እነዚህ ወረዳዎች፤ ባህር ዳር ዙሪያ፣ ሰሜን ሜጫ፣ ደቡብ ሜጫ፣ ሰሜን አቸፈር እና ደቡብ አቸፈር በሚል የመዋቅር ስያሜ የሚታወቁት ናቸው። 

በአንጻራዊነት ለባህር ዳር ከተማ ቅርበት የሌላቸው የአዲሱ ዞን ወረዳዎች፤ ጎንጅ ቆላላ እና ይልማና ዴንሳ የተሰኙት ናቸው። የአብዛኞቹ ወረዳዎች ከባህር ዳር በቅርብ ርቀት መገኘት፤ የአዲሱን ዞን መቀመጫም በከተማዋ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል። 

የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊም ወረዳዎቹ በባህርዳር ከተማ ዙሪያ ስለሚገኙ “automatically መቀመጫቸውን ባህር ዳር ማድረጋቸው የማይቀር ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከምዕራብ ጎጃም ዞን ተለይቶ የሚቋቋመው ዞንን ስያሜ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ግዛቸው፤ “ስያሜውን የሚወስነው አዲስ የሚደራጀው ዞን ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)