በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፤ በክልሉ ስር ያለው የመተከል ዞን መልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ስራ በፌደራል መንግስት “በቂ ትኩረት አልተሰጠውም” ሲል ቅሬታውን ገለጸ። የፌደራሉ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ለደረሰው ውድመት በሰጠው ትኩረት እና የሀብት አመዳደብ ልክ ለመተከል ዞንም ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ ፓርቲው ጠይቋል።
ቦዴፓ ይህን የገለጸው የመተከል ዞንን መልሶ ግንባታ እና የማቋቋም ስራን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 16፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። ክልላዊ ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ ከሚያዝያ 2011 ጀምሮ በመተከል ዞን ባለው ግጭት እና አለመረጋጋት የበርካታ ዜጎች ህይወት መቀጠፉን እና ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የዞኑ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ጠቅሷል። በግጭቱ ሳቢያ በትምህርት በጤና፣ በውሃ ተቋማት፤ በኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች እንዲሁም መንገዶች ላይ “ከፍተኛ ውድመት” መድረሱንም ፓርቲው በመግለጫው አስታውሷል።
በመተከል ዞን የደረሰውን ከፍተኛ ውድመት መልሶ የመተካት፣ ተፈናቃዮችን የማቋቋም፣ ተጎጂዎችን የመደገፍ እና መንግስታዊ አገልግሎት የማስጀመር ስራውን በዋነኛነት ማከናወን የሚገባው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት መሆኑን የጠቆመው ቦዴፓ፤ ሆኖም በዞኑ ያለው ችግር “በመደበኛው አሰራር በተፈለገው ደረጃ ይፈታል” የሚል እምነት እንደሌለው አስታውቋል። በመተከል ዞን ያለውን “ከባድ ችግር” ለመፍታት “የተለየ በጀት እና የሰው ኃይል” መመደብ እና “ለዚሁ ተግባር የሚውል አደረጃጀት” መዘርጋት ያስፈልጋል ብሏል ፓርቲው።
በመተከል ዞን ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስፈልገው ስራ “በክልሉ መንግስት አቅም ብቻ” እንደማይፈጸም ያመለከተው ቦዴፓ፤ በመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ስራ የፌደራል መንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል። የፌደራል መንግስት በዞኑ ለደረሰው ውድመት የሰጠው ትኩረት “በቂ አይደለም” የሚለው ፓርቲው፤ ለሰሜን ኢትዮጵያ በተሰጠው “ትኩረት እና የሀብት አመዳደብ” ያህል ለመተከል ዞንም “በተመሳሳይ በቂ ትኩረት ሰጥቶና ሀብት መድቦ” ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።
የፌደራል መንግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን በ2015 በጀት ዓመት መልሶ ለማቋቋም ከመንግስት ግምጃ ቤት 20 ቢሊዮን ብር መድቧል። በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ግንባታ የሚውል 300 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ ከዓለም ባንክ እንደተገኘ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ግንቦት ወር አስታውቆ ነበር። ድጋፉ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተመረጡ ወረዳዎች ለሚደረጉ የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ስራዎች የሚውል መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።
የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ለሚደረጉ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክቶች አገልግሎት ቢሮ ጋር የሶስተኛ ወገን የትግበራ ስምምነት ባለፈው ሐምሌ ወር መፈራረሙም ይታወሳል። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)