የሲዳማ ክልል ምክር ቤት፤ በክልሉ ተግባራዊ የሚደረገውን የዞን አደረጃጀት በዚህ ሳምንት ሊያጸድቅ ነው

በሃሚድ አወል

ከምስረታው ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ያለ ዞን መዋቅር የቆየው የሲዳማ ክልል፤ አራት ዞኖች እና አንድ የከተማ አስተዳደር የሚኖሩትን አዲስ አደረጃጀት በዚህ ሳምንት በሚደረገው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ሊያጸድቅ ነው። በአዲሱ የዞን አደረጃጀት ላይ በቅርቡ ውይይት ያደረገው የሲዳማ ክልል መንግስት ካቢኔ፤ መዋቅሩ ይጸድቅ ዘንድ ለክልሉ ምክር ቤት ማስተላለፉን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በሰኔ 2012 በይፋ የተመሰረተው የሲዳማ ክልል፤ በነባር አወቃቀሩ 30 ወረዳዎች እና ሰባት የከተማ አስተዳደሮችን የያዘ ነው። ክልሉ የበጀት ክፍፍል ሲያደርግም ሆነ ሌሎች መስተጋብሮችን ሲያካሄድ የቆየው፤ ከእነዚህ ወረዳዎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በቀጥታ በመገናኘት ነበር። የሲዳማ ክልልን በዞን እና በከተማ አስተዳደር የማዋቀር ሂደትን የተመለከተ ጥናት፤ ክልሉ ከመመስረቱ በፊት ቢደረግም ተግባራዊ ሳይደረግ እስካሁን መቆየቱን ሁለት የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ የዞን መዋቅሩ ተግባራዊ ሳይሆን የቆየው፤ አዲሱ ክልል “በሁለት እግሩ እስከሚቆም ድረስ ሌሎች አደረጃጀቶችን እናቆይ ተብሎ ነው” ሲሉ እስካሁን የዘገየበትን ምክንያት አስረድተዋል። የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም በበኩላቸው “[ክልሉ] አዲስ አደረጃጀት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ቢያንስ ሀገራዊ ሁኔታው እስኪረጋጋ እና የክልሉ አደረጃጀትም መሬት እስከሚረግጥ የሌላ መዋቅር ጥያቄ ይቆይ” የሚል ውሳኔ ከዚህ ቀደም ተላልፎ እንደነበር አስታውሰዋል። 

በዚህ ውሳኔ መሰረት የሲዳማ ክልል በነባር አወቃቀሩ ስር ካሉት ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች ጋር በቀጥታ ግንኙነት ሲያደርግ በመቆየቱ፤ ለዞኖች ይመደብ የነበረውን ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን አቶ ፊሊጶስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በክልሉ እና በወረዳዎች መካከል የዞን መዋቅሮች አለመኖር በመደበኛ ስራዎች ላይ ጫና መፍጠሩን ግን የጽህፈት ቤት ኃላፊው አልሸሸጉም።

“መሃል ላይ ወረዳዎችን በቅርበት የሚደግፍ ዞን ካለመኖሩ የተነሳ፤ የክልል ቢሮዎች እስከታች ድረስ ወርደው ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ አለባቸው። ይሄ ደግሞ በክልል ቢሮዎች ላይ ጫና ፈጥሯል” ሲሉ በሲዳማ ክልል የዞን አደረጃጀት ባለመኖሩ ምክንያት የነበረውን ችግር አቶ ፊሊጶስ አብራርተዋል። ፌዴሬሽኑን በመቀላቀል አስረኛ የሆነው የሲዳማ ክልል፤ ቅድሚያ የሰጣቸውን የክልል ማደራጀት ስራዎች ካጠናቀቀ በኋላ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ ዞን መዋቅር ማዞሩን የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ይናገራሉ።   

የሲዳማ ክልል የዞን መዋቅርን በተመለከተ በተካሄደው ጥናት ላይ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲያደርግ መቆየቱንም ኃላፊዎቹ አክለዋል። በእነዚህ ውይይቶች ክልሉ የ“አቅጣጫ ስያሜ” ያላቸው አራት ዞኖች እንዲኖሩት ከስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል። ከአራቱ ዞኖች በተጨማሪም ክልሉ አንድ የከተማ አስተዳደር እንዲኖረው ከውሳኔ ላይ መደረሱንም አክለዋል።  

አዲስ የሚመሰረቱት አራት ዞኖች ሰሜን ሲዳማ፣ ምስራቅ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ሲዳማ እና ደቡባዊ ሲዳማ የሚሉ መጠሪያዎች እንዷላቸው የሲዳማ ክልል ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እነዚህ ዞኖች መቀመጫቸውን በሐዋሳ፣ ይርጋለም፣ አለታ ወንዶ እና ዳዬ ከተሞች እንደሚያደርጉም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል። ሐዋሳ ከተማ ከዞን ማዕከልነት በተጨማሪ ራሱን የቻለ የከተማ አስተዳደር ሆኖ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። 

በሲዳማ ክልል ህገ መንግስት መሰረት ተጠሪነቱ ለክልሉ መንግስት የሆነው የሐዋሳ ከተማ፤ የራሱ የአስተዳደር ምክር ቤት ይኖረዋል። ከነገ በስቲያ ረቡዕ ነሐሴ 18 ጀምሮ ለሶስት ቀናት መደበኛ ጉባኤውን በሚያካሄደው የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አደረጃጀታቸው ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አራቱ አዳዲስ ዞኖች ግን የየራሳቸው ምክር ቤቶች አይኖራቸውም ተብሏል። 

የሲዳማ ክልል የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ “በክልሉ በተለየ በወረዳ ወይም በአካባቢ የተደራጀ ብሔረሰብ የለም። ሲዳማ homogenous [ማህበረሰብ] ነው። ዋና ተግባርን የሚፈጽመው ወረዳ [ደግሞ] የራሱ ምክር ቤት አለው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የዞን አስተዳደሮች በክልሉ ርዕስ መስተዳደር ስር የተደራጁ አስፈጻሚ አካል መሆናቸው በሲዳማ ክልል ህገ መንግስት ላይ ተደንግጓል። የዞኖች አስተዳዳሪ እና ምክትል አስተዳዳሪን ጨምሮ የዞን አመራሮች ተመርጠው የሚሾሙት በክልሉ ርዕስ መስተዳድር ሲሆን የአስተዳዳሪው ተጠሪነትም ለክልሉ ርዕስ መስተደዳር ነው። የዞን ዋና አስተዳዳሪን ስልጣን የሚዘረዝረው የህገ መንግስቱ ክፍል “የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር በመወከል ዞኑን ያስተዳድራል እንዲሁም ስራዎችን ይመራል” ይላል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)