ምርጫ ቦርድ፤ የጋራ ክልል ለመመስረት ጥያቄ ያቀረቡ የደቡብ ክልል መዋቅሮች ውሳኔ እንዲላክለት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጠየቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ወስነው ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲልክለት ጠየቀ። ምርጫ ቦርድ በሶስት ወራት ጊዜ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ በምክር ቤቱ የተላለፈው ውሳኔን በተመለከተ ደግሞ፤ የህዝበ ውሳኔ መርኃ ግብር የማዘጋጀት ስልጣን የቦርዱ በመሆኑ በዚሁ አግባብ የጊዜ ሰሌዳውን ወደ ፊት እንደሚገልጽ አስታውቋል።

ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 17 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ነው። ቦርዱ በዚሁ ደብዳቤው፤ በደቡብ ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የጋራ ክልል መመስረትን በተመለከተ በየምክር ቤቶቻቸው ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ህዝበ ውሳኔ ለማደራጀት ለቦርዱ በግብዓትነት የሚያገለግል መሆኑን ጠቅሷል።

ዞኖቹ እና ልዩ ወረዳዎቹ ይህንኑ ውሳኔያቸውን ለማስፈጸም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር አያይዘው የሏኳቸው ሰነዶችም ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ለሚደረገው ዝግጅት የሚያስፈልጉ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ አመልክቷል። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረቡለትን ጥያቄዎች እና ተያያዥ ሰነዶች ለቦርዱ እንዲልክ በደብዳቤው ተጠይቋል።

በደቡብ ክልል የሚገኙት የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖችን እንዲሁም የደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ ቡርጂ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች፤ በጋራ አንድ ክልል ለመመስረት በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁትን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገቡት ከ20 ቀናት በፊት ሐምሌ 28፤ 2014 ነበር። ዞኖቹ እና ወረዳዎቹ የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለውን ይህን ውሳኔ በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁት ሐምሌ 23 እና 24፤ 2014 ባካሄዷቸው ስብሰባዎች ናቸው። 

ምርጫ ቦርድ በዚሁ ደብዳቤ ያነሳው ሌላው ጉዳይ ህዝበ ውሳኔው የሚደረግበትን የጊዜ ማዕቀፍ በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ያሳለፈው ውሳኔ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 12፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ምርጫ ቦርድ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ መወሰኑ ይታወሳል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ “ቀን ቆጥሮ” የሰጠበትን አካሄድ፤ ቦርዱ “አግባብነት ካላቸው የህግ ማዕቀፎች አንጻር” በጥልቀት መመርመሩን በደብዳቤው አስታውቋል። በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ምርጫዎች እና ህዝበ ውሳኔዎች የሚካሄዱበትን የመርኃ ግብር ሰሌዳ የማውጣት ስልጣን “የተቋሙ ብቻ መሆኑን” ቦርዱ በአጽንኦት ገልጿል። 

“ቦርዱ የተቋቋመበትን አላማ ለማስፈጸም ከተቋማዊ እና መዋቅራዊ ነጻነት በተጨማሪ በህግ ተለይተው የተሰጡትን ስልጣን እና ኃላፊነቶች በተመለከተ የሚኖረው የውሳኔ እና የስራ አፈጻጸም ነጻነት ሁሌም መከበር ይኖርበታል” ሲልም ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው አሳስቧል። 

ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 የወጣው የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ የቦርዱን ስልጣን እና ተግባር በሚዘረዝረው ክፍል፤ “በየደረጃው የሚካሄዱ ምርጫዎች መርኃ ግብር ሰሌዳ እንዲዘጋጅ ማድረግ፣ ማጽደቅ እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻልና መፈጸሙን መከታታል” የቦርዱ ስልጣን እና ተግባር መሆኑን ይደነግጋል። በዚሁ መሰረት ቦርዱ ለህዝበ ውሳኔው አፈጻጸም የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ሰሌዳ አውጥቶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚገልጽ በደብዳቤው አስታውቋል።

“ቦርዱ የተቋቋመበትን አላማ ለማስፈጸም ከተቋማዊ እና መዋቅራዊ ነጻነት በተጨማሪ በህግ ተለይተው የተሰጡትን ስልጣን እና ኃላፊነቶች በተመለከተ የሚኖረው የውሳኔ እና የስራ አፈጻጸም ነጻነት ሁሌም መከበር ይኖርበታል”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከጻፈው ደብዳቤ የተወሰደ

የጊዜ ሰሌዳው የሎጂስቲክስ ዝግጅት ለማድረግ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ለመልመል እና ለመመደብ፣ ምርጫ ጣቢያዎች ለማደራጀት እና ለታዛቢዎች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ይሆናል ብሏል ቦርዱ። ምርጫ ቦርድ በዚሁ ደብዳቤው በህዝበ ውሳኔ ላይ የሚያገባቸውን ባለድርሻ አካላት የማወያየት እቅድ እንዳለው ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)