በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ዳግም ውጊያ መቀስቀሱ ተነገረ

የህወሓት አማጺ ቡድን ዛሬ ንጋት ከለሊቱ 11 ሰዓት ላይ በምስራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብል እና በተኩለሽ አቅጣጫዎች “ጥቃት መፈጸሙን” እና “የተኩስ ማቆሙን” በይፋ ማፍረሱን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። የትግራይ ሰራዊት ወታደራዊ ኮማንድ የተባለው አካል በበኩሉ ዛሬ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በሰባት አካባቢዎች ውጊያ እንደነበር ገልጾ፤ ጥቃቱን የጀመረው ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው ሲል ወንጅሏል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 18፤ 2014 ባወጣው መግለጫ፤ “የህወሓት ታጣቂ ቡድን” ጥቃት የከፈተው “ከመንግስት በኩል የቀረቡለትን በርካታ የሰላም አማራጮች ሁሉ ወደጎን በመተው” መሆኑን ገልጿል። የህወሓት ታጣቂ ቡድን “የፈጸመው ጥቃትም ሆነ እሱን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ አስቀድሞ ለትንኮሳው ሲዘጋጅ እንደነበር ግልጽ ማሳያ ነው” ሲልም የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ ከስሷል። 

ዛሬ የተቀሰቀሰውን ውጊያ በተመለከተ በትግራይ ቴሌቪዥን በተላለፈ “ሰበር ዜና” መረጃውን በቅድሚያ ያወጣው የትግራይ ሰራዊት ወታደራዊ ኮማንድ የተባለው አካል ነው። የወታደራዊ ኮማንዱ በዚሁ መግለጫው፤ በጩቤ በር፣ ጃኖራ፣ ጉባጋል፣ አላማጣ፣ ባላ፣ ባሶ በር “መጠነ ሰፊ ጥቃት” እንደተከፈተበት አስታውቆ ነበር።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ፤ የመከላከያ ሰራዊት እና የጸጥታ ኃይሎች ከህወሓት ታጣቂ ቡድን “የተሰነዘረባቸውን ጥቃት በተቀናጀ መልኩ በድል እየመከቱት ይገኛሉ” ብሏል። ህወሓት “ከውጪ ደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ጦርነቱን የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎትን ሲያንጸባርቅ ቆይቷል” ያለው የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ፤ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ “የትግራይን ወጣት ለማስጨረስ ሕወሓት የሚያደርገውን የጦርነት ጉሰማ እንዲያቆም ጠንካራ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል” ሲል ጥሪውን አቅርቧል። 

የፌደራል መንግስት ካለፈው መጋቢት አጋማሽ ጀምሮ “ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን” ማስታወቁ ይታወሳል። ከዚያን ወቅት ጀምሮ በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ አማጽያን መካካል የነበረው ውጊያ ጋብ ብሎ ነበር። ሁለት ዓመት ሊሞላው ወራት የቀሩትን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፌደራል መንግስት ባለፈው ሰኔ ወር ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙ ይታወሳል።

የፌደራል መንግስት የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 11፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊያመጣ የሚችል የሰላም ምክረ ሀሳብ ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጎ ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ የተዘጋጀው የሰላም ምክረ ሃሳቡ “በተቻለ ፍጥነት ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ” መወሰኑንም በወቅቱ ተገልጿል።

የሰላም ንግግሩ “በአስቸኳይ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ዘንድ” ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ኮሚቴው ማስታወቁ ይታወሳል። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው መግለጫው፤ የፌደራል መንግስት “ዛሬም ነገም የሰላም አማራጭ የመጀመሪያ መፍትሔ እንደሆነ ፅኑ እምነት አለዉ” ሲል አቋሙን አንጸባርቋል። 

በፌደራል መንግስት በኩል “የሰላም አማራጭ የመጀመሪያ መፍትሔ” እንደሆነ ቢጠቀስም፤ “የሽብር ቡድን” ተብሎ በመግለጫ የተጠራው ህወሓት “ወደደም ጠላም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ለማድረግ ግን አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ” እንደሚወሰድ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። መንግስት እርምጃውን የሚወስደው “ሀገር የማዳን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ስላለበት ነው” መሆኑንም በመግለጫው ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)