የአፍሪካ ህብረት፣ ተመድ፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ፤ በኢትዮጵያ ውጊያ ቆሞ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቀረቡ

የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ በኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ውጊያ እንዳሳሰባቸው ስጋታቸውን ገለጹ። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና የብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ትላንት ረቡዕ በተናጠል ውጊያ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ለአምስት ወራት ገደማ ጋብ ብሎ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ትላንት ረቡዕ ነሐሴ 18፤ 2014 ዳግም ማገርሸቱ ከተሰማ በኋላ፤ ከዓለም አቀፍ ማህብረሰቡ ስጋት የተጫናቸው ድምጾች ተደምጠዋል። ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ለ21 ወራት ገደማ የተዋጉት የፌደራል መንግስት እና ህወሓት፤ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማበጀት ድርድር ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም ሁለተኛ ዙር ጦርነት መቀስቀሱ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን አሳስቧል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ትላንት ረቡዕ ምሽት ባወጡት መግለጫ፤ በፌደራል መንግስት እና ትግራይን በሚያስተዳድረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ዳግም ውጊያ መቀስቀሱ በጥልቅ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሁለቱን ኃይሎች እንዲያሸማግሉ የሾሙት ሊቀመንበሩ፤ ተኩስ ቆሞ ሁለቱ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ንግግር እንዲጀምሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ለኢትዮጵያ ጥቅም ሲባል በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሂደትን ለመደገፍ የአፍሪካ ህብረት አሁንም ከሁለቱም ወገኖች ጋር በጥምረት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ማህማት በመግለጫቸው አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጋር እንዲወያዩም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ዳግም ውጊያ በመጀመሩ “መደናገጣቸውን እና ማዘናቸውን” ገልጸዋል። ትላንት ረቡዕ ባወጡት መግለጫ “ኢትዮጵያውያን በበቂ ተሰቃይተዋል” ያሉት ጉቴሬዝ፤ እንደ ሙሳ ፋኪ ማህማት ሁሉ ውጊያ ቆሞ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት የሰላም ንግግር እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል። እገዛ ለሚያሻቸው ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲረጋገጥ እና መሰረታዊ አገልግሎቶች ስራ እንዲጀምሩም ጉተሬዝ አሳስበዋል።

ውጊያው በተጀመረበት በትላንትናው ዕለት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ የሚገኝ የዓለም የምግብ ፕሮግራም መጋዘን መዘረፉን ጉተሬዝ የሚመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ገልጾ ነበር። የትግራይ ኃይሎች በመቐለ ከተማ ወደ የሚገኝ የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) መጋዘን በኃይል ገብተው፤ በአስራ ሁለት የነዳጅ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች የተጫነ 570,000 ሊትር ነዳጅ መውሰዳቸውን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት በቦታው የነበሩ የዓለም የምግብ ድርጅት ሰራተኞች “ዘረፋውን” ለማስቆም ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። ይህ የነዳጅ ክምችት ምግብ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ለማሰራጨት  ብሎም ለሰብዓዊ ግልጋሎት ብቻ ሊውል የታቀደ እንደነበር ዱጃሪች ገልጸዋል። 

ትላንት የተፈጸመው ዘረፋ “በሰሜን ኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን የሚረዱ የግብረ ሰናይ ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” ሲሉም ቃል አቃባዩ አክለዋል። “ሰብዓዊ ቁሳቁሶችን እና የግብረ ሰናይ ተቋማትን ቅጥር ግቢ ዘረፋ ወይም በኃይል አስገድዶ መውሰድ እናወግዛለን” ያሉት የተመድ ቃል አቀባይ፤ ሁሉም ወገኖች የግብረ ሰናይ ሰራተኞችን፣ እንቅስቃሴዎቻቸውን እና ንብረታቸውን ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ሕግ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩ አሳስበዋል።  

እንደ አፍሪካ ህብረት እና ተመድ ሁሉ የአውሮፓ ህብረትም በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልጿል።   የአውሮፓ ህብረት የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ያገረሸው ግጭት በሰላም ተስፋ ላይ ጥላውን እንደሚያጠላ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ግጭቱ “ወደ ሙሉ ጦርነት ከመቀየሩ በፊት” ሁለቱ ወገኖች ሁኔታውን ሊያረግቡ እንደሚገባ ያሳሰቡት ቦሬል፤ “ለሰላም ንግግር ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዓለም አቀፍ ተቋማቱ ኃላፊዎች በኩል በተመሳሳይ መልኩ የተንጸባረቀው ስጋት፤ የአሜሪካ እና የብሪታንያ ዲፕሎማቶችንም የተጫነ ሆኗል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ውይይታቸውን ወደ ፊት ለማራመድ ጥረታቸውን በእጥፍ አሳድገው ያለ ቅድመ ሁኔታ ከዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደርሱ እና በቋሚነት ለግጭቱ መቋጫ እንዲያበጁ ጥሪ አቅርበዋል።  

ከመጋቢት 2014 አጋማሽ ወዲህ ከአምስት ወራት በላይ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ገቢራዊ ያደረጉት “ለሰብዓዊነት ሲባል የግጭት የማቆም ውሳኔ” ግጭትን ሁከት መቀነሱን በመግለጫቸው የጠቀሱት ብሊንከን፤ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰዋል።  “የዚህ የተኩስ አቁም ላለፉት አምስት ወራት መከበር የበርካቶችን ሕይወት ታድጓል፤ በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎችም እገዛ እንዲደርስ ረድቷል” ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ። 

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጊያ አውድማዎች የተከሰተው መተነኳኮስ፣ ጠብ ጫሪ ንግግሮች እና የዘላቂ ተኩስ አቁም አለመኖር ለታየው መሻሻል መልሰው እንከን መሆናቸውን ብሊንከን ትላንት ረቡዕ ምሽት ባወጡት በመግለጫቸው አንስተዋል። እንደ አዲስ ያገረሸው ግጭት እና በአዲስ አበባ እና በመቐለ መካከል የሚታየው የቃላት መወራወር፤ በአገሪቱ አካታች የፖለቲካ ሂደት ለመመስረት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያዘገይም የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጠቁመዋል። 

የሁለቱ ተፈላሚ ወገኖች ወደ ውጊያ መመለስ፤ የኢትዮጵያን ዜጎች ለመጠነ ሰፊ ስቃይ፣ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ እና ለተጨማሪ የኢኮኖሚ ፈተና እንደሚዳርግ ብሊንከን አስጠንቅቀዋል። ይህ ሁኔታ “የኢትዮጵያን ሰላም እና ጸጥታ ለማደፍረስ ከሚፈልጉ እጅ” አገሪቱን ሊጥል እንደሚችልም አሳስበዋል።

የብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ በበኩላቸው የጦርነቱ ዳግም መቀስቀስ “የሰብዓዊ ሁኔታውን አስከፊነት ያባብሳል” ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ውጊያ አቁመው ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማበጀት ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ሊመለሱ ይገባል ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)