በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

በሃሚድ አወል

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለሚቀጥለው ሳምንት አርብ ነሐሴ 27፤ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ። በተመስገን ላይ የቀረበውን ክስ እየተመለከተ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን የሚሰጠው፤ በዐቃቤ ህግ የሰነድ ማስረጃዎች እና የተከሳሽ ጠበቆች በማስረጃዎቹ ላይ ያቀረቡትን አስተያየት ከመረመረ በኋላ ነው። 

የፌደራል ዐቃቤ ህግ ባለፈው ሰኔ ወር በተመስገን ደሳለኝ ላይ ለመሰረታቸው ሶስት ክሶች፤ በ“ፍትሕ” መጽሔት ላይ የወጡ 17 ጽሁፎችን በማስረጃነት አቅርቦ ነበር። በ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ላይ የቀረቡት ክሶች “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለህዝብ በመግለጽ”፣ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት” እንዲሁም “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር” የመፈጸም ወንጀሎች ናቸው።

ዐቃቤ ህግ ባቀረባቸው ማስረጃዎች ላይ የጋዜጠኛው ጠበቆች አስተያየታቸውን በጽሁፍ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ያቀረቡት ከሁለት ሳምንት በፊት ባለፈው ነሐሴ 4፤ 2014 ነበር። ችሎቱ በዐቃቤ ህግ ማስረጃዎች እና በጠበቆች አስተያየት ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 19 ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

በዛሬው የችሎት ውሎ “የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ብዛት እንዳላቸው” የገለጸው፤ ፍርድ ቤቱ በዚህም ምክንያት ለብይን ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል። በዚህም መስረት ለሚቀጥለው ሳምንት አርብ ነሐሴ 27 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። 

የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ በአካል ተገኝቶ የተከታተለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ አሁን በእስር ላይ በሚገኝበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ያልተፈታለትን አቤቱታ ለችሎቱ አቅርቧል። የተመስገን ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ አቤቱታውን ለችሎቱ ያቀረቡት “በማረሚያ ቤቱ መፍትሔ አይሰጣችሁም ተብለናል” በማለት ነበር። 

ተመስገን ያቀረበው አቤቱታ፤ በሳምንት አምስት ቀን ቤተሰብ ምግብ እንዲያስገቡለት፤ የሚተኛበት ክፍል ውስጥ ወንበር እንዲገባለት እና ሽፍን ጫማ ማድረግ እንዲፈቀድለት የሚጠይቅ ነው። አቤቱታውን የተቀበለው ፍርድ ቤቱ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተያየቱን በመጪው ነሐሴ 24፤ 2014 በጽሁፍ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)