በመቐለ የተዘረፈው 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንዲመለስ የኢትዮጵያ መንግስት ጠየቀ

የኢትዮጵያ መንግስት በትላንትናው ዕለት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ከሚገኝ የዓለም የምግብ ድርጅት መጋዘን በህወሓት ኃይሎች የተዘረፈው 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንዲመለስ ጠየቀ። ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ወደ ትግራይ የሚገባው ሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖረው ህዝብ እየደረሰ መሆኑን እና ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማስተማመኛ እንዲሰጥም ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቧል።

የፌደራል መንግስት ይህን ያስታወቀው በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በኩል ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 19፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ በዚሁ መግለጫው፤ “ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም የገባን የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ለወታደራዊ ዓላማ ማዋሉን ቀጥሏል” ሲል ከስሷል። 

ለዚህ ማሳያው ለሰብዓዊ አቅርቦት በሚውል የነዳጅ እና የምግብ እርዳታ ላይ በትላትናው ዕለት በመቐለ የተፈጸመው ዝርፊያ እንደሆነ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ ጠቅሷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች ትላንት ምሽት በሰጡት መግለጫ፤ በመቐለ ከተማ ወደ የሚገኝ የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) መጋዘን በኃይል የገቡ ትግራይ ኃይሎች፤ በ12 የነዳጅ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች የተጫነ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መውሰዳቸውን አስታውቀው ነበር። 

ድርጊቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ የዓለም የምግብ ድርጅት ሰራተኞች ዘረፋውን ለማስቆም ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱንም የተመድ ቃል አቃባይ ገልጸዋል። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው መግለጫው፤ የህወሓት ቡድን ከፈጸመው ዘረፋ ባሻገር “ድርጊቱን ለማስቆም የሞከሩ የሰብዓዊ እርዳታ ባለሙያዎችንም አስሯል” ሲል ወንጅሏል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ አክሎም “የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የቀረበላቸውን ማስረጃ ከግምት በማስገባት በሽብር ቡድኑ ላይ ግልጽ የሆነ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍኑ” በዛሬው መግለጫው ጠይቋል። የተመድ ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪች በትላንትና ምሽት መግለጫቸው፤ “ሰብዓዊ ቁሳቁሶችን እና የግብረ ሰናይ ተቋማትን ቅጥር ግቢ ዘረፋ ወይም በኃይል አስገድዶ መውሰድ እናወግዛለን” ብለው ነበር። ሁሉም ወገኖች የግብረ ሰናይ ሰራተኞችን፣ እንቅስቃሴዎቻቸውን እና ንብረታቸውን ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ሕግ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩም ቃል አቃባዩ አሳስበዋል።


የመቐለውን የዓለም የምግብ ድርጅት መጋዘን ዝርፊያ ተከትሎ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ፤ “የተሰረቀው ነዳጅ አሁኑኑ እንዲመለስ እንሻለን” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕከት አስታውቀው ነበር። ዋና ዳይሬክተሩ “በትግራይ ባለስልጣናት” ተፈጸመ ያሉትን የነዳጅ ስርቆት “የሚያስቆጣ” እና “አሳፋሪ” ሲሉ ኮንነውታል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)