በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ የስራ ማቆም እና ከቤት ያለመውጣት አድማ ተደረገ

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል በሚገኘው የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ፤ ለሁለተኛ ጊዜ የስራ ማቆም እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መደረጉን የከተማይቱ ነዋሪዎች ገለጹ። የአድማው መንስኤ ከጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የደቡብ ክልል ኮማንድ ፖስት ትላንት ባወጣው መግለጫ የንግድ ሱቆችን መዝጋት እና የትራንስፖርት አገልግሎትን ማቋረጥ “በጥብቅ የተከለከለ” መሆኑን ቢያስታውቅም፤ በወልቂጤ ከተማ ይታይ የነበረው የወትሮ እንቅስቃሴ ዛሬ ቆሞ መዋሉን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል። እነዚሁ ነዋሪዎች በከተማይቱ የሚገኙ የንግድ ሱቆች እና ባንኮች ዝግ ሆነው መዋላቸውን አስረድተዋል።

አቶ ሠንብት ነስሩ የተባሉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ የጸጥታ ኃይሎች ዛሬ ረፋድ ላይ ያልተከፈቱ የንግድ ሱቆችን ሲያሽጉ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የደቡብ ክልል ኮማንድ ፖስት በወልቂጤ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በኩል ትላንት አመሻሽ ላይ ላይ ባወጣው መግለጫ “የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ በሚተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ” አስጠንቀቅቆ ነበር።

በወልቂጤ ከተማ ዛሬ ስራ አቁመው ከነበሩት የመንግስት እና የግል ድርጅቶች በተጨማሪ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ተቋርጦ መዋሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በከተማይቱ አውራ ጎዳናዎች የሚታዩት የጸጥታ ኃይሎችን የያዙ ተሸከርካሪዎች ብቻ መሆናቸውንም አስረድተዋል። 

በከተማይቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የስራ መቆም አድማ የተደረገው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። ለነሐሴ 3፤ 2014 የተጠራውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የከተማይቱ የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ቆሞ እንደነበር የከተማይቱ ነዋሪዎች በወቅቱ ገልጸው ነበር። በማህበራዊ ሚዲያ የተጠራው የዛሬው አድማ ነገን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማይቱ ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ለአድማው መንስኤ የሆነው የጉራጌ ዞንን በአጎራባች ከሚገኙ አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር፤ “በክላስተር” በአንድ ክልል ለማደራጀት በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ነው። ይህ የውሳኔ ሃሳብ ከጉራጌ ፖለቲከኞች እና “አክቲቪስቶች” ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ነሐሴ 5፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤም፤ ይህንኑ የ“ክላስተር” አደረጃጃት በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

በደቡብ ክልል ጉዳይ ባለፈው ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባውን ያደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የጉራጌ ዞንን ጨምሮ ሌሎች አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል እንዲቀጥሉ ወስኗል። በነባሩ ክልል የሚቀጥሉት የስልጤ፣ ሀላባ፣ ሀድያ እና ከንባታ ጠንባሮ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ናቸው።

ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባው ስድስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በጋራ ክልል ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ አስተላልፏል። በህዝበ ውሳኔ አዲሱን “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን” የሚመሰረቱት የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖችን እንዲሁም የደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ ቡርጂ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)