ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የወሰን ማካለል በአስቸኳይ እንዲቆም አሳሰቡ

በሃሚድ አወል

ሶስት ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ “ሂደቱን ያልጠበቀ፣ ህግን ያልተከተለ” ነው ያሉትን የአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል እንዲቆም አሳሰቡ። ፓርቲዎቹ ጉዳዩ “በሀገራዊ ምክክሩ ሊፈታ ይገባል” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይህን አቋማቸውን ዛሬ አርብ ነሐሴ 20፤ 2014 በጋራ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት፤ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና እናት ፓርቲ ናቸው። ፓርቲዎቹ በዛሬ መግለጫቸው በዋናነት ያነሱት ጉዳይ፤ ከአስር ቀናት በፊት ይፋ የሆነው በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን አከላለልን ተግባራዊ ለማድረግ የተደረሰውን ስምምነት ነው።

የእናት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያየህ አስማረ “አዲስ አበባ ብዙ ጊዜ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ እየተደረገች ነው ያለችው። ይህቺን ከተማ ሚና ቢስ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ አይቶ ዝም ማለት ስለማይቻል ነው ይኼንን መግለጫ ያወጣነው” ሲሉ ፓርቲዎቹ የዛሬውን መግለጫ የሰጡበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ሶስቱ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልል መንግስት በኩል የተፈጸመውን የወሰን ማካለል ስምምነት፤ የአዲስ አበባን “ነዋሪዎች አልፎም መላው ኢትዮጵያውያንን የሚያውክ አካሄድ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። የወሰን ማካለሉ ስምምነት “የቦታ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚታይበት መንገድ ፈጽሞ ስህተት ነው” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ውሳኔው “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱን ነዋሪዎች መብት የሚጥስ ድርጊት ነው” ሲሉ ተችተዋል።  

ስምምነቱ “ሂደቱን ያልጠበቀ” እና “ህግን ያልተከተለ” ነው የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ ተፈጸመ ላሉት የህግ ጥሰት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ተጠያቂ አድርገዋል። ጉዳዩ ወደፊት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሀገራዊ መግባባት ውይይት “አንድ ጉዳይ ሆኖ እንዲታይ ማድረግና መፍታት ሲገባ በይድረስ ይድረስ በገዢው ፓርቲ እየተፈጸመ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።

የእናት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያየህ፤ የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ በሀገራዊ ምክክሩ ከሚፈቱ “ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ” ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። “የብሔራዊ ምክክሩ አጀንዳዎችን እያመጡ ፖለቲካዊ ውሳኔ መወሰን ችግሩን የከፋ ያደርገዋል እንጂ አይፈታውም” ሲሉ በሶስቱ ፓርቲዎቹ መግለጫ ላይ የተነሳውን ሃሳብ አስተጋብተዋል። 

መኢአድን ወክለው በመግለጫው የተገኙት የፓርቲው የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታጠቅ አሰፋ በበኩላቸው፤ ወሰን ማካለሉ ይፈጥራቸዋል ያሏቸውን ችግሮች አንስተዋል። አቶ ታጠቅ “ከመሬቱ ጋር አብረው ተወስደዋል” ያሏቸው “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ” የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል “ሲካለሉ” “አስተዳደራዊ ችግሮች ይመጣሉ” ባይ ናቸው።  

የመኢአድ የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ ያጋጥማሉ ያሉትን ችግር ሲያብራሩ “ኦሮምኛ መጻፍም፣ የመናገርም፣ የማዳመጥም ችሎታ የሌላቸው ሰዎች በአንድ ጀምበር ተለቅመው ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄዱ። ሁሉም ነገር አገልግሎት የሚያገኙት በኦሮምኛ ነው ማለት ነው”  ብለዋል። አቶ ታጠቅ ይህን ይበሉ እንጂ፤ የወሰን ማካለል ስምምነቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት “የሚሰጡ መንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ቋንቋ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ ይደረጋል” ብለው ነበር።

ከንቲባዋ የወሰን ማካለሉ በአገልግሎት ላይ ተፅዕኖ እንደማይፈጥር ማስተማመኛ ቢሰጡም፤ ፓርቲዎቹ ግን በመግለጫቸው “በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ይካሔዳል የተባለው ሂደቱን ያልጠበቀ፣ ሕግን ያልተከተለ የወሰን ማካለል በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ሶስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የወሰን ማካለሉ እንዲቆም ከማሳሰብ በተጨማሪ የመንግስት ባለስልጣናት ሕዝቡን ወደ ግጭት የሚመሩ ንግግሮችን እና እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)