የሲዳማ ክልል አዲስ ያዋቀራቸውን አራት አዳዲስ ዞኖች ለማደራጀት የ150 ሚሊዮን ብር በጀት አጸደቀ

በሃሚድ አወል

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አዲስ ለተዋቀሩ አራት አዳዲስ ዞኖች ማደራጃ የሚሆን 150 ሚሊዮን ብር አጸደቀ። የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 21፤ 2014 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ፤ ክልሉን በአራት ዞኖች የሚያዋቅረውን አዋጅም በሁለት ድምጸ ተዐቅቦ አጽድቋል።

የሲዳማ ክልል ከምስረታው በኋላ ያሉትን ሁለት ዓመታት ያለዞን መዋቅር ነበር ያሳለፈው። ክልሉ የበጀት ክፍፍል ሲያደርግ የቆየውም በስሩ ካሉት 30 ወረዳዎች እና ሰባት የከተማ አስተዳደሮች ጋር በቀጥታ በመገናኘት ነበር። በትላንትናው ዕለት በተጀመረው እና ዛሬ በተጠናቀቀው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ፤ ለ2015 በጀት ዓመት ለክልሉ የጸደቀው 19.9 ቢሊዮን ብር ሆኗል።

የሲዳማ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አራርሶ ገረመው፤ ለአራቱ አዲስ ዞኖች የተመደበው በጀት በዋናነት ለደመወዝ እንዲሁም የቢሮ ቁሳቁሶች ለማሟላት ይውላል ብለዋል| ፎቶ፦ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ -አማርኛ ልሳን

ከዚህ በጀት ውስጥ 0.75 በመቶ የሚሆነውን፤ ለአዲሶቹ ዞኖች ማደራጃ እንዲሆን ክልሉ መድቧል። የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አራርሶ ገረመው፤ ለዞኖቹ የተመደበው በጀት በዋናነት ለደመወዝ እንዲሁም የቢሮ ቁሳቁሶች ለማሟላት እንደሚውል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለዞኖቹ የሚከፋፈሉ ተሽከርካሪዎች ግዢም በዚህ በጀት ስር የሚካተት እንደሆነ አስረድተዋል።      

“[የዞን] የስራ ሴክተሮቻችንን በዘርፍ ለይተን ነው የምንመራው” የሚሉት ዶ/ር አራርሶ፤ ለዞኖቹ የተመደበው በጀት በእነዚህ ዘርፎች ላይ ለሚቀጠሩ ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች ደመወዝ ክፍያ እንደሚሆን ገልጸዋል። የሲዳማ ክልል ዞኖቹን በዚህ መልክ ለማደራጀት በጀት ቢመድብም፤ ለወረዳዎች እና ለከተማ አስተዳደሮች ሲያደርግ የቆየው የበጀት ክፍፍል ግን በነበረበት እንደሚቀጥል የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ጠቁመዋል።  

የሲዳማ ክልል በጀት ድልድልን በተመለከተ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲከተለው የቆየውን አሰራር የቀጠለበት ምክንያት፤ ከአዲሶቹ አራት ዞኖች አወቃቀር ጋር የተያያዘ ነው። በሲዳማ ክልል ህገ መንግስት መሰረት የዞን አስተዳደሮች በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ስር የተደራጁ አስፈጻሚ አካል ናቸው። የዞኖች አስተዳዳሪ እና ምክትል አስተዳዳሪን ጨምሮ የዞን አመራሮች ተመርጠው የሚሾሙት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነው።

በሲዳማ ክልል ህገ መንግስት መሰረት የዞን አስተዳዳሪዎች እና ምክትል አስተዳዳሪዎች ጨምሮ የዞን አመራሮች ተመርጠው የሚሾሙት በክልሉ ርዕስ መስተዳድር ነው | ፎቶ፦ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ -አማርኛ ልሳን

የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ከዞኖች ይልቅ ለወረዳዎች በቀጥታ በጀት የሚመደብበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “ዞን ምክር ቤት አይኖረውም። የእኛ ዞኖች ማስተባበሪያ ዞኖች ነው የሚሆኑት። ወረዳዎችን ይከታተላሉ፤ ለክልሉ ሪፖርት ያቀርባሉ። በጀቱ እየጸደቀ የሚሰራው ግን በወረዳዎች [ነው]። ምክር ቤት ያላቸው ወረዳዎች ስለሆኑ በዚያ አግባብ ነው የምንተገብረው” ሲሉ አብራርተዋል። 

የሲዳማ ክልል ለ2015 በጀት ዓመት፤ ለወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የመደበው በጀት 8.9 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው። ይህ ገንዘብ ከአጠቃላይ የክልሉ በጀት 44.8 በመቶ ያህል ድርሻ አለው። የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ካጸደቀው የክልሉ በጀት ውስጥ፤ ለክልሉ መንግስት መቀመጫ ለሆነችው ሐዋሳ ከተማ የመደበው 3 ቢሊዮን ብር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)