በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምረው ኮሚሽን፤ በሀገሪቱ ዳግም ግጭት መቀስቀሱ እንዳሳሰበው ገለጸ

በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመው ኮሚሽን አባላት የሆኑ ሶስት የህግ ባለሙያዎች፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች መካከል ዳግም ግጭት መቀስቀሱ “አስቆጥቶናል” አሉ። ይህ አይነቱ ውጊያ በአካባቢው የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች ያለባቸውን ችግር የበለጠ እንደሚያባብስም ገልጸዋል።

ሶስቱ የህግ ባለሙያዎች ይህን ያሉት በጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት በኩል ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 23፤ 2014 ባወጡት መግለጫ ነው። የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎቹ መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ዳግም ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የሰነበተውን ስጋት አስተጋብቷል። 

የትግራይ ክልልን ከአማራ እና አፋር ክልሎች ጋር በሚያዋስኑ ቦታዎች ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የተቀሰቀሰው ሶስተኛ ዙር ውጊያ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ውግዘት ገጥሞታል። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት ባለፈው ሐሙስ በሰጡት መግለጫ፤ የውጊያው ዳግም መቀስቀስ እንዳሳሰባቸው ገልጸው ግጭቱ “አንገብጋቢ እርዳታ የሚፈልጉ ሰላማዊ ሰዎችን ስቃይ እንደሚያባብስ” አስጠንቅቀው ነበር። 

ባቼሌት የሚመሩት ኮሚሽን የሾማቸው፤ ሶስት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችም በዛሬው መግለጫቸው ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎቹ “በመቐለ ከተማ በሚገኝ የመጫወቻ ቦታ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ስለ መድረሱ የተሰማው ሪፖርት እና በአማራ ክልል በቆቦ እንደ አዲስ የተጀመረው ማጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ አነጣጥሯል መባሉ” በተለይ እንዳሳሰባቸው በመግለጫቸው ጠቁመዋል። 

“የሰላማዊ ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች፣ ጤና እና ደህንነት የሁሉም ወገኖች ቀዳሚ ጉዳይ መሆን አለበት” ያሉት ባለሙያዎቹ፤ የመንግስታቱ ድርጅት እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በትግራይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ክፍፍሉን እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት እንዲወስዱ አሳስበዋል። በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ውጊያ ተባብሶ የመቀጠል አደጋ ማዘሉን በመግለጫቸው የጠቆሙት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች፤ ተፈላሚ ወገኖች “በአፋጣኝ ውጊያቸውን አቁመው ወደ ውይይት እንዲመለሱ” ጥሪ አቅርበዋል። 

ከሚያዝያ 24፤ 2013 ወዲህ በኢትዮጵያ በሁሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የሚባሉ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የስደተኞች እና የሰብዓዊ ሕግጋት ጥሰቶችን የመርመር ስልጣን የተሰጠው የባለሙያዎች ኮሚሽን ሶስት አባላት አሉት። ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ በሊቀመንበርነት በሚመሩት በእዚህ የባለሙያዎች ኮሚሽን ውስጥ አሜሪካዊው ስቴቨን ራትነር እና ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኮማራስዋሚ በአባልነት ተካትተዋል። 

ሶስቱ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች፤ ባለፈው ሐምሌ ወር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል። ባለሙያዎቹ ወደ አዲስ አበባ ከመጓዛቸው አንድ ወር አስቀድመው ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን መመርመር መጀመራቸውን አስታውቀው ነበር። በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን መቀመጫውን ያደረገውን በዩጋንዳ ኢንቴቤ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)