በቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ የቢሮ ኃላፊ የባንክ አካውንት፤ 8.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ተደርጎ እንደነበር ፖሊስ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ለሚገኙት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቢሮ ኃላፊ፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ 8.5 ሚሊዮን ብር በባንክ አካውንታቸው ገቢ እንደተደረገላቸው የፌደራል ፖሊስ ገለጸ። በዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ስም ከተከፈቱ አራት የባንክ አካውንቶች፤ 6.4 ሚሊዮን ብሩ ወጪ መደረጉንም አስታውቋል። 

የፌደራል ፖሊስ ይህን የገለጸው “በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በሚገኙት ዶ/ር ሙሉቀን ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማከናወን ዛሬ ሰኞ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ባቀረበበት ወቅት ነው። ፖሊስ በተጠርጣሪው ስም በተከፈቱ የባንክ አካውንቶች የተደረጉ ዝውውሮችን መረጃ ያገኘው ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት መሆኑን የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን እየተመለከተ ለሚገኘው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ፖሊስ ባለፈው ቀጠሮ በተፈቀዱለት 14 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማድመጥ ነበር። በጽህፈት ቤት በኩል ለተሰየመው ለዚሁ ችሎት የፌደራል ፖሊስ ባቀረበው ገለጻ፤ በተፈዱለት የምርመራ ቀናት የአራት ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት የኦዲት ሪፖርት መቀበሉን እንዲሁም የተጠርጣሪውን የባንክ ሂሳብ ዝውውር መረጃ ማግኘቱን አስረድቷል።

የፌደራል ፖሊስ ቀጣይ ይቀሩኛል ያላቸውን ተግባራት ለማከናወን 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀዱለት ችሎቱን ጠይቋል። በዶ/ር ሙሉቀን የባንክ ሂሳብ የተካሄደው የገንዘብ ዝውውር በማን እንደተከናወነ መረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልጉት ለችሎት የገለጸው ፖሊስ፤ ሌሎች ተጨማሪ ተግባራት እንደሚቀሩትም አስረድቷል። 

ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ከጠየቀባቸው ምክንያቶች ውስጥ “ያለ አግባብ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ የወጣላቸውን ግለሰቦች መለየት” እና “ከተጠርጣሪው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጣራት” የሚሉት ይገኙበታል። ከተጠርጣሪው ቤት የተያዙ በተባሉ “ሶፍትዌር” እና “ዲቫይስ” ላይ ትንተና ማድረግ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኦዲት ሪፖርት ማምጣት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ መረጃዎች ማስመጣት ሌሎች ቀሪ ስራዎች በሚል በፖሊስ የተዘረዘሩ ናቸው።

ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን ወክለው ችሎት የተገኙት ሁለት ጠበቆች፤ በፖሊስ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጥያቄ ተቃውመዋል። ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት አቶ አድያም ሰገድ አጥናፉ፤ “ከዚህ በፊት በነበሩት ቀጠሮዎች፤ ለቀጠሮ መጠየቂያ የቀረቡ ምክንያቶች ያለምንም ለውጥ በድጋሚ ቀርበዋል” ሲሉ ተከራክረዋል።

እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ከተጠርጣሪው ጋር በቀጥታ ያላቸው ግንኙነት አለመጠቀሱን ያነሱት የተጠርጣሪው ጠበቃ፤ ፖሊስ የዘረዘራቸው ምክንያቶች ደንበኛቸውን ማረፊያ ቤት ለማቆየት በቂ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። “መረጃ ይመጣባቸዋል” የተባሉት ተቋማት “ጠንካራ ቁጥጥር እና አሰራር ያላቸው” መሆናቸውን በማንሳትም፤ ደንበኛቸው በዋስ ቢወጡ ምርመራውን እንደማያደናቅፉት አቶ አድያም ሰገድ ለችሎቱ አስረድተዋል።

በጠበቆች ለቀረበው መቃወሚያ የፌደራል ፖሊስ በሰጠው ምላሽ፤ ዶ/ር ሙሉቀን ከእስር ቢለቀቁ “ምስክር ያባብሉብናል፣ ያሸሹብናል። ከነበራቸው ኃላፊነት አንጻር ቀሪ ማስጃዎችን ሊያበላሹብን ይችላሉ። የተፈጸመው ወንጀልም ከባድ በመሆኑ ሊቀርቡ አይችሉም” ሲል ተሟግቷል። “የተጠርጣሪው በእስር መቆየት ምርመራውን የበለጠ ስለሚያጠናክርልን ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው ይከታተሉ” ሲል አስተያየቱን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። 

የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ ከጠየቀው 14 የምርመራ ቀናት አስራ አንዱን ቀናት በአብላጫ ድምጽ ፈቅዷል። በዛሬው የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከተገኙ ሶስት ዳኞች መካከል አንደኛው ዳኛ “ለፖሊስ የምርመራ ቀናት ሊፈቀድ አይገባም” በሚል የልዩነት ሃሳባቸውን አቅርበዋል። 

ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ያቀረባቸው ምክንያቶች “ከዚህ በፊት በነበረው ቀጠሮ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲቀርቡ የነበረ እና የምርመራ ቀናት ሲሰጥባቸው የነበሩ ናቸው” ያሉት ዳኛው፤ ፖሊስ ያቀረባቸው ምክንያቶችም “በቂ እና አሳማኝ” አይደሉም ብለዋል። “ፖሊስ ተጠርጣሪው በወንጀል ድርጊቱ ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ እና በእርሳቸው ላይ ያሰባሰባቸውን ማስረጃዎች አላቀረበም” ሲሉም አክለዋል። 

ዳኛው ይህን ቢሉም፤ ፖሊስ በዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ላይ ለሚያደርገው ምርመራ፤ ለአራተኛ ጊዜ ተጨማሪ ቀናት ተፈቅዶለታል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ያከናወናቸውን ተግራት ለማድመጥ ለጷጉሜ 4፤ 2014 ቀጠሮ በመስጠት የዛሬ ውሎውን አጠናቅቋል። ላለፈው አንድ ወር ከ15 ቀናት በእስር ላይ የቆዩት ዶ/ር ሙሉቀን ዛሬ ለአራተኛ ጊዜ በችሎት ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ የአዲስ አበባ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ሙሉቀን፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት “በስልጣን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” ተጠርጥረው ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)