ሳፋሪኮም የሙከራ አገልግሎቱን በድሬዳዋ ጀመረ

በኢትዮጵያ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በማቅረብ የመጀመሪያው የግል ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም፤ የሙከራ አገልግሎቱን ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 23፤ 2014 በድሬዳዋ ከተማ ጀምሯል። ሳፋሪኮም ዛሬ የጀመረው የሙከራ አገልግሎት፤ የኩባንያውን ሲምካርዶች የሚገዙ ተጠቃሚዎች በ2G፣ 3G እና 4G ኔትወርኮች የድምጽ፣ የጽሁፍ መልዕክቶች እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ማግኘት የሚያስችላቸው ነው።

በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተባባሪ ዘጋቢ ዛሬ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ጀምሮ ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የሳፋሪኮም ቅርንጫፎች፤ የኩባንያውን አገልግሎት መጠቀም የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ሲምካርዶችን ሲገዙ አስተውሏል። በሳቢያን፣ ከዚራ እና ኮኔል በሚባሉ የከተማይቱ አካባቢዎች የሚገኙት የኩባንያው ቅርንጫፎች፤ በምሳ ሰዓት ጭምር አገልግሎት ሲሰጡም ታዝቧል። 

በሁሉም የኩባንያው ቅርንጫፎች የሳፋሪኮም ሲም ካርድ እየተሸጠ ያለው በ30 ብር ነው። ሳፋሪኮም ሲም ካርዶቹን ለሚገዙ አዲስ ደንበኞች፤ የ5፣ 10፣ 15፣ 25፣ 50 እና 100 ብር ዋጋ ያላቸው የአየር ሰዓት ካርዶች ያዘጋጁ ሲሆን የኩባንያውን መለያዎች የያዙ መደበኛ እና “ስማርት” ስልኮችንም ለሽያጭ አቅርቧል። ኩባንያውን አገልግሎት በአማራጭነት ለመጠቀም ያሰቡ ተገልጋዮች፤ ሁለት ሲምካርዶች በሚቀበሉ የሞባይል ስልኮቻቸው የሳፋሪኮምን ሲምካርድ በተጨማሪነት አስገብተው ሲሞክሩ ታይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)