በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀስ አዲስ ክልላዊ ፓርቲ፤ የምስረታ ጉባኤውን አካሂዶ ሊቀመንበሩን መረጠ

በሃሚድ አወል

የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) የተሰኘ አዲስ ክልላዊ ፓርቲ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 23፤ 2014 ባካሄደው መስራች ጉባኤው፤ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትን አቶ ተሰማ ኤሊያስን በሊቀመንበርነት መረጠ። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲው በዛሬው ጉባኤው፤ የፓርቲውን ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ያጸደቀ ሲሆን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫንም አካሂዷል። 

የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ ምዝገባ ፈቃድ ያገኘው ከሶስት ወራት በፊት ግንቦት 11፤ 2014 ነበር። ሲፌፓ የመስራች ጉባኤውን ከማካሄዱ በፊት ለአባልነት ፍላጎት ያሳዩ 30 ሺህ ገደማ የሲዳማ ክልል ነዋሪዎችን መዝግቦ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት አቶ ተሰማ ኤልያስ፤ በስተመጨረሻ ፓርቲው በአባልነት የተቀበላቸው ግን አምስት ሺህ ግለሰቦችን ብቻ ነው ብለዋል። 

ፎቶ:- የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት፤ በክልል ደረጃ የሚመሰረት ፓርቲ አራት ሺህ መስራች አባላት እንደሚያስፈልጉት ይደነግጋል። ከፓርቲው መስራች አባላት ውስጥ ከ60 በመቶው በላይ የክልሉ መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸውም አስፍሯል። በዛሬው የሲፌፓ መስራች ጠቅላላ ጉባኤ የተገኙ አባላት ብዛት 320 እንደሆነ ፓርቲው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ በዘለቀው በዛሬው የሲፌፓ መስራች ጉባኤ፤ ፓርቲውን ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚመሩ ሊቀመንበር እና ሁለት ምክትል ሊቀመናብርት ምርጫ ተካሄዷል። ፓርቲውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ ተሰማ፤ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን በማራመድ ስማቸው በጉልህ ከሚነሱ “አክቲቪስቶች” መካከል የሚጠቀሱ ነበሩ።

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በሀዋሳ እና በሲዳማ የተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሰው የነበሩ ሁከቶችን በማስተባበር ከተጠረጠሩ ሌሎች ዘጠኝ ግለሰቦች ጋር ለዘጠኝ ወራት ታስረው ከቆዩ በኋላ ክሳቸው ተቋርጦ ተፈትተዋል። አቶ ተሰማ የሲዳማ ክልል በይፋ ከተመሰረተ ወዲህም ለሁለት ጊዜያት ያህል ታስረዋል። የአዲሱ ፓርቲ ተመራጭ ሊቀመንበር፤ የቅርብ ጊዜያቶቹ እስራቸው “ከፖለቲካ አቋም ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ነው” ባይ ናቸው።

ፎቶ:- የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ

የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ በዛሬው የመስራች ጉባኤው፤ አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶን የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አድርጎ መርጧል። አቶ ደሳለኝ ደምሴ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር እና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።  ሶስቱ የፓርቲው አመራሮች፤ 13 አባላት ባሉት የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴን ተቀላቅለዋል። 

በዛሬው የሲፌፓ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ብቸኛ ሴት ተመራጭ የሆነችው ወ/ሪት ሙሉ ጋላሳ ነች። የፓርቲው የሴቶች እና ወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ሰብሳቢ የሆነችው ወ/ሪት ሙሉ፤ 45 አባላት ባሉት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴም ብቸኛዋ ሴት አባል ሆናለች።

የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተሰማ፤ ቀዳሚው ተግባር “የፖርቲውን መዋቅር መዘርጋት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ፓርቲው የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ ሰርተፊኬት ለማግኘት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ እንደሚያስገባም ተናግረዋል። የሲፌፓ አመራር ፓርቲውን ከማደራጀት ባሻገር “ጎን ለጎን የሚሰራቸው ክልላዊ እና ሀገራዊ አስቸኳይ ጉዳዮች” እንዳሉትም አቶ ተሰማ ጠቁመዋል።  

ፎቶ:- የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ

ሲፌፓ “አንገብጋቢ” ከሚላቸው ክልላዊ ጉዳዮች መካከል “ትልቁ” በሲዳማ የሚታየው “የስራ አጥነት ቀውስ” እንደሆነ የፓርቲው ተመራጭ ሊቀመንበር ገልጸዋል። “ይህ ስራ አጥነት የመልካም አስተዳደር እጦት ነው” የሚሉት አቶ ተሰማ፤ በክልሉ በስፋት ይታያል የሚሉት ይህ ችግር የፓርቲያቸው ቀጣይ ዋነኛ አጀንዳ ይሆናል ብለዋል። 

ፓርቲው በፖለቲካው ዘርፍ ያለውን ዕቅድ በተመለከተ ደግሞ፤ ሲፌፓ የፌደራሊዝም አቋም ካላቸው በሀገር ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ “በሀገር ደረጃ የመንቀሳቀስ” እቅድ እንዳለው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሲዳማ በህዝበ ውሳኔ የራሱን ክልል ቢመሰርትም “ራሱን በራስ ማስተዳደር የሚባለው ነገር በተገቢው መንገድ አልተመለሰም” የሚል እምነት ያላቸው አቶ ተሰማ፤ ህዝቡ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አመልክተዋክል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)