በኢትዮጵያ ዳግም በተቀሰቀሰው ውጊያ ሳቢያ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ተጠልለው የነበሩ 30 ሺህ ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ። በተመሳሳይ ሁኔታ በአፋር ክልል ካሉ ሶስት ወረዳዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ሪፖርት እንደደረሰው የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል።
የተመድ ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪች ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 24 ምሽት በሰጡት ዕለታዊ መግለጫቸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት በመቀጠሉ ሁኔታ በአካባቢው ያለው ሁኔታ ውጥረት የተሞላበት እንደሆነ ተናግረዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች እየተፈናቀሉ ነው መባሉ፤ የሰብዓዊ መብት ፍላጎትን እንደጨመረውም ጠቁመዋል።
ቃል አቃባዩ በዚሁ መግለጫቸው፤ የአፋር ክልል ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው ቦታዎች በሚገኙት በያሎ እና ጉሊና ወረዳዎች እየተካሄደ ባለው ውጊያ ሳቢያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ሪፖርት መደረጉን ጠቅሰዋል። በአፋር እና አማራ አዋሳኝ ቦታ በሚገኘው ጭፍራ ወረዳም፤ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የሚያመለክት ሪፖርት እንዳለ ዱጃሪች ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ውጊያ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ በተባለ የተፈናቃዮች መጠለያ ተጠልለው የነበሩ 30 ሺህ ሰዎችም ዳግም ለመፈናቀል መዳረጋቸውን ዱጃሪች በመግለጫቸው አንስተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አጋሮቹ “የጸጥታው ሁኔታ” በፈቀደ መጠን፤ በሰሜን ኢትዮጵያ እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
ቃል አቃባዩ በዚሁ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች እና ለወታደራዊ ዓላማ ለማይውሉ ቦታዎች “የማያቋርጥ ጥንቃቄ” እንዲያደርጉ በመግለጫቸው አሳስበዋል። ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ ጋር በሚስማማ መልኩ፤ ሰላማዊ ሰዎች ጉዳት ወደማይደርስባቸው ቦታዎች እንዲሄዱ ሊፈቅዱላቸው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዱጃሪች በትላንቱ መግለጫቸው በትግራይ ክልል ስላለው የእርዳታ አቅርቦትም አንስተዋል። ቃል አቃባዩ፤ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረውን የምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶች ስርጭት እንደገና ጀምረዋል ብለዋል። ዱጃሪች ይህን ቢሉም፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከትላንት በስቲያ ሰኞ በሰጠው መግለጫ ግን በየብስ እና በአየር ወደ ክልሉ የሚጓጓዘው እርዳታ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ መቋረጡን አስታውቆ ነበር።
ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ለማድረስ ወደዚያ የሚወስደው መንገድ ተከፍቶ እንደው ከጋዜጠኛ ጥያቄ የቀረበላቸው የተመድ ቃል አቃባይ፤ መንገዱ “አሁንም ዝግ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)