የትግራይ ኃይሎች ከአማራ ክልል እንዲወጡ የብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጠየቁ

የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል የሚያደርጉትን ውጊያ አቁመው ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለሱ የብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ጠየቁ። ሚኒስትሯ በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ኃይሎች ክልሉን ለቀቅው መውጣት አለባቸው ብለዋል። 

ቪኪ ፎርድ ይህን ያሉት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች ዳግም ወደ ግጭት መመለሳቸውን በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 26፤ 2014 ባወጡት መግለጫ ነው። ሁለቱ ኃይሎች እንደገና ወደ ግጭት መግባታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ “መከራ የሚያመጣ” ነው ያሉት የብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር፤ በክስተቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን የማጣት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ገልጸዋል። 

በሁለቱ ኃይሎች ውጊያ ምክንያት በቀጥታ ከሚደርሰው የሰዎች ሞት ባሻገር፤ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኘው ሰብዓዊ ሁኔታ በግጭቱ ምክንያት ይበልጥ ስለሚባባስ የሰዎችን ሞት ሊያስከትል እንደሚችል ፎርድ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር የሚገኙ 13 ሚሊዮን ሰዎችን የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ እንዳደረጋቸው ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ የአሁኑ ውጊያ እና በህወሓት የተያዘው የዓለም የምግብ ድርጅት ነዳጅ፤ የሰብዓዊ ድርጅቶችን ስራ “ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል” ብለዋል።

የብሪታንያ መንግስት፤ ህወሓት የያዘውን ነዳጅ ለእርዳታ ማከፋፈል እና ለሌሎች አንገብጋቢ አገልግሎቶች እንዲውል እንዲያደርግ ጥሪ ያቀርባል ሲሉም የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትሯ አክለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶቹን በአስቸኳይ ወደነበሩበት እንዲመለሱ እንዲያደርግ የብሪታንያ መንግስት ተመሳሳይ ጥሪ እንደሚያቀርብም ፎርድ በመግለጫቸው አስፍረዋል።    

የብሪታንያ መንግስት ከዚህ በተጨማሪም በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ውጊያ በማቆም፤ ገደብ የለሽ የሰብዓዊ እርዳታ የሚቀርበብትን ሁኔታ እንዲያረጋግጡ አሳስቧል። ዓለም አቀፍ ውግዘት የበረታበት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም የተቀሰቀሰው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 18፤ 2014 ነበር። አንድ ሳምንት ላስቆጠረው ለዚህ ውጊያ መቀስቀስ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ።   

በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀሰቀሰው ውጊያ 22 ወራት ማስቆጠሩን በዛሬው መግለጫቸው የጠቀሱት ቪኪ ፎርድ፤ ለችግሩ “ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለ ግልጽ ሆኗል” ሲሉ ጉዳዩ በንግግር ሊፈታ የሚገባ እንደሆነ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሮ የነበረው የግጭት ማቆም ስምምነት ግጭቱን በፖለቲካዊ መንገዶች ለመፍታት ዕድል ፈጥሮ እንደነበር የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትሯ በዛሬው መግለጫቸው አስታውሰዋል። 

አሁን የተቀሰቀሰው ውጊያ “ወደ ሰላም የሚወስደውን መንገድ የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል” ያሉት ፎርድ፤ ንግግሮች ቢጀመሩ ሰላም ለማስፈን የሚረዱ መሻሻሎች ይታያሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ንግግሮች ይጀመሩ ዘንድ፤ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል የሚያደርጉትን ውጊያ አቁመው ወደ ትግራይ እንዲመለሱ ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አሳስበዋል። የኤርትራ ኃይሎችም የትግራይ ክልልን ለቅቀው እንዲወጡ በተመሳሳይ መልኩ ጥሪ አቅርበዋል። 

“ይህን ግጭት ለመፍታት ያለው ብቸኛ መንገድ የግጭት ማቆሙን ወደነበረበት መመለስ እና የፖለቲካዊ ድርድር ወዲያውኑ መጀመር ነው። በዚህ ረገድ የአፍሪካ ህብረትን የማሸማገል ጥረቶች እንደግፋለን። የግጭቱን የበለጠ መባባስ ለመቀልበስ፤ እነዚህን ጥረቶች በእጥፍ መጨመር እንደሚገባ እናሳስባለን” ሲሉ የብሪታንያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትላንት ምሽት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። በኢትዮጵያ ላለው ግጭት ዘላቂ መቋጫ ለማበጀት፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ጥረቶቻቸውን የበለጠ ማሳደግ  እንደሚገባቸው የገለጹት ብሊንከን፤ ሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ ዘመቻቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)