የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የፍርድ ቤት ክርክር ለመጪው ዓመት ተሸጋገረ

በተስፋለም ወልደየስ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎች ላይ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን አስተያየት እና ዐቃቤ ለአስተያየቱ የሰጠውን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 10፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኛው ካለበት የጤና ችግር በተያያዘ እንዲፈቀዱለት የጠየቃቸው ጉዳዮች በማረሚያ ቤት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የቀረበውን ክስ በመመልከት ላይ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ለዛሬ አርብ ነሐሴ 27፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ዐቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ባያያዛቸው የሰነድ ማስረጃዎች ላይ የተከላካይ ጠበቆች በጽሁፍ ያቀረቡትን አስተያየት መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር። ሆኖም የፌደራል ዐቃቤ ህግ ከቀጠሮው ሶስት ቀናት አስቀድሞ ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፤ በጠበቆች  አስተያየት ላይ መልስ መስጠት እንዲችል ይፈቀድለት ዘንድ በመጠየቁ፤ ችሎቱ በዛሬው ውሎ ይህንኑ ጉዳይ ወደ መመልከት ዞሯል።

የፌደራል ዐቃቤ ህግ በዚሁ ደብዳቤው፤ ተከሳሽ በቀረቡበት የሰነድ ማስረጃዎች ላይ “መስቀለኛ ምዘና” በማድረግ ባለ 13 ገጽ አስተያየት ለፍርድ ቤት ማስገባቱን አስታውሷል። ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ በጠበቆች አስተያየት ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አለመስጠቱንም ጠቅሷል። በጉዳዩ ላይ በጹሁፍ ምላሽ ለመስጠት እንዲፈቀድለት በዚሁ ደብዳቤ የጠየቀው ዐቃቤ ህግ፤ ይህ መደረጉም “ለትክክለኛ የፍትህ አሰጣጥ ይረዳል” ብሏል። 

ችሎቱ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ከመግባቱ በፊት፤ ዐቃቤ ህግ ይህንኑ ደብዳቤ ለተከሳሽ ባለበት ማረሚያ ቤት አድርሶ እንደሆነ ጥያቄ አቅርቧል። ጋዜጠኛ ተመስገን ደብዳቤው እንዳልደረሰው በመግለጹ፤ ችሎቱ የማጣሪያ ጥያቄዎችን ለዐቃቤ ህግ ሰንዝሯል። ዐቃቤ ህግ ደብዳቤው በመዝገብ ቤት እንደተላከ ለፍርድ ቤት ቢያስረዳም፤ ለዚሁ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ በችሎቱ የቀረበለትን ጥያቄ በማስረጃ ማስደገፍ ሳይችል ቀርቷል።

ይህንኑ ተከትሎ ፍርድ ቤቱ፤ ዐቃቤ ህግ በደብዳቤ ያቀረበውን አቤቱታ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን እና ሁለቱ ጠበቆቹ በዚያው በችሎት እንዲመለከቱ አድርጓል። በደብዳቤው ይዘት ላይ ከደንበኛቸው ጋር ለደቂቃዎች የተመካከሩት ጠበቆች፤ በዐቃቤ ህግ አቤቱታ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በተከታታይ ለችሎት አሰምተዋል። 

ከተከሳሽ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ቤተማርያም አለማየሁ፤ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበው አቤቱታ “ስነ ስርዓታዊ ያልሆነ ነው” ሲሉ ተቃውመዋል። በዐቃቤ ህግ የሚቀርቡ የሰው ማስረጃዎች በመስቀለኛ ጥያቄ እንደሚፈተሹ ሁሉ፤ የሰነድ ማስረጃዎች ደግሞ በተከሳሽ ወገን በሚቀርቡ አስተያየቶች የሚመዘኑበት ስርዓት እንዳለ ጠበቃው ለፍርድ ቤት አስረድተዋል። ሆኖም በዚህ መልክ በሚቀርቡ አስተያየቶች ላይ “ዐቃቤ ህግ አስተያየት እንዲሰጥ የሚፈቀድበት ስርዓት የለም” ሲሉ አቶ ቤተማርያም ተሟግተዋል። 

የተከሳሽ ጠበቃ በሁለተኛነት ያነሱት መከራከሪያ፤ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታ “ቅን ልቦና የጎደለው” እና “የክስ መዝገቡን ሂደት ለማዘግየት ያለመ ነው” የሚል ነው። ለዚህም ጠበቃው በአስረጂነት ያነሱት ነጥብ፤ ዐቃቤ ህግ አቤቱታውን ያቀረበው የሰነድ ማስረጃው አስተያየት ከደረሰው ከ20 ቀን በኋላ መሆኑን ነው። አቤታቱው ለፍርድ ቤቱ የደረሰው ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ሁለት ሶስት ቀን ሲቀረው መሆኑን ጠበቃው በተጨማሪነት ጠቅሰዋል።

ዐቃቤ ህግ ይህን ቀን መርጦ ያደረገው፤ ዳኞች ፍርድ ቤት ዘግተው ለእረፍት የሚወጡበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ እና “ብይን ሳይሰጥ መዝገቡ ለመጪው ዓመት እንዲሻገር በማሰብ ነው” ሲሉ አቶ ቤተማርያም ተከራክረዋል። “አንድ ተከራካሪ በቅን ልቦና ማጣት ምክንያት መዝገቡ እንዲሻገር ሊያደርግ አይገባውም። የእዚህ ችሎት remote control ያለው በዳኞች እጅ ነው። ማንም ከውጭ ሆኖ ሊቆጣጠረው አይገባም” ያሉት ጠበቃው፤ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግን አቤቱታ ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። 

የጋዜጠኛ ተመስገን ሌላኛው ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ አሁን በአቤቱታው ላይ ያቀረበውን ጉዳይ፤ የሰነድ ማስረጃ ጉዳይ በተነሳባቸው ከዚህ ቀደም በነበሩ ሁለት የችሎት ውሎዎች ላይ አለማንሳቱን አስታውሰዋል። “በከሳሽ በኩል ያለው ፍላጎት የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ሂደቱን ማጓተት እና ደንበኛችን ሳይፈረድበት ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ ማድረግ ነው” ያሉት ጠበቃ ሄኖክ፤ “ቀጠሮው እንዲጓተት ማድረግ የህግ መሰረት የሌለው ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ ነው” ሲሉ ተሟግተዋል። 

ጋዜጠኛ ተመስገን የጤና ችግር እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት ጠበቃው፤ በክረምት ወቅት የደንበኛቸውን የጤና ሁኔታ በሚያባብስ ሁኔታ በማረሚያ ቤት መቆየት እንደሌለበት ተናግረዋል። ደንበኛቸው “የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት” እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ሄኖክ፤ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግን አቤቱታ ውድቅ አድርጎ ጠበቆች ባቀረቡት የሰነድ ማስረጃ አስተያየት ላይ ብይን አዘጋጅቶ ከሆነ ይህንኑ በዛሬው ዕለት በንባብ እንዲያሰማ ጠይቀዋል። ብይኑ ካልተጠናቀቀ ግን ለመጪው ሰኞ ነሐሴ 30 ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል።  

ሁለቱ ጠበቆቹ ያቀረቧቸውን መከራከሪያዎች ተከትሎ ጋዜጠኛ ተመስገን የመናገር ዕድል እንዲሰጠው ጠይቆ በችሎቱ ተፈቅዶለታል። በአቤቱታው ደብዳቤ ላይ እርሱን በተመለከተ የቀረበው “የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመተላለፍ” እንደሆነ የጠቀሰው ጋዜጠኛው፤ ከዚህ ቀደምም ዐቃቤ ህግ “መከላከያ ሰራዊት በተደጋጋሚ ጊዜ አስጠንቅቆታል” በማለት በችሎት መናገሩን አስታውሷል። 

“ሁላችንም እንደምናውቀው የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ካጠፉ በህግ ይጠየቃሉ። የሰሩት ወንጀልም ካለ በሚዲያ ይጋለጣሉ። ሆኖም ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበው በህግ የማይጠየቁ፣ የማይከሰሱ አድርጎ ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ የገለጸው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ ዐቃቤ ህግ “የመከላከያ ሰራዊትን ተገን አድርጎ” እንዲህ አይነት ገለጻዎችን በተደጋጋሚ የሚጠቀመው “እኔን በእስር ቤት ለማቆየት ነው” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል። 

የተከሰሰበትን ጉዳይ የሚመለከተው ችሎት “በነጻነት ይሰራል” ብሎ እንደሚያምን ለዳኞች የተናገረው ተመስገን፤ ሆኖም እርሱ በእስር እንዲቆይ የመከላከያ አመራሮች ከኋላ “ተጽዕኖ ያደርጋሉ” የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል። በዛሬው ችሎት ከተሰየሙ ሶስት ዳኞች መካከል የመሃል ዳኛው የተከሳሹን ንግግር አቋርጠው “ይህን ያስባልዎት ነገር ምንድንነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። 

“ዐቃቤ ህግ ከዚህ በፊት ባቀረበው አቤቱታ ላይ ‘በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶታል’ ማለቱ ምን ማለት እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። በወቅቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አልወሰድኩትም እንጂ ከዚህ ቀደም አንድ የመከላከያ ሰራዊት መኮንን ‘የተናደደ ወታደር እርምጃ ሊወስድበት ይችላል’ ብለዋል” ሲል ምክንያቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ለዚህ የተመስገን አስተያየት የመሃል ዳኛው በሰጡት ምላሽ “ዳኛ የሚዳኘው በህግ እና ህግ ብቻ ነው። ተጠያቂነቱም ለህሊናው ብቻ ነው” ብለዋል። 

ዳኛው ከዚህ በማስከተልም፤ በተከሳሽ ወገን በኩል ለቀረቡ መከራከሪያዎች ዐቃቤ ህግ ምላሽ እንዲሰጥ ዕድሉን ሰጥተዋል። የሰነድ ማስረጃ የሚፈተሽበት ስርዓት በወንጀል “ስነ ስርዓት ህጉ ላይ አልተደነገገም” ያለው ዐቃቤ ህግ፤ ሆኖም ይህንኑ የሚከለክል አንቀጽ ባለመኖሩ ጠበቆች አስተያየት ለማቅረብ እንደተፈቀደላቸው በምላሹ ላይ አስገንዝቧል። ጠበቆች ባቀረቡት አስተያየት ላይ ዐቃቤ ህግ ምላሽ የመስጠት “ስነስርዓታዊ መብት” እና “አመክንዮአዊ ምክንያት” እንዳለውም ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

በክርክር መርህ መሰረት፤ ክርክርን የሚጨርሰው የጀመረው መሆኑን የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ ጠበቆች “ባቀረቡት አስተያየት ላይ የመጨረሻ ተናጋሪ መሆን አለብን” ሲል ለችሎቱ አቤት ብሏል። ጠበቆች ባቀረቡት አስተያየት ላይ “መልስ ሳንሰጥ ብንቀር የክርክሩን ሂደት ይጎዳል” ያለው ዐቃቤ ህግ፤ ከዚህ በኋላ ባለው ሂደት አስተያየቱን “መሞገት የሚችልበት ሌላ ዕድል” ስለሌለ ፍርድ ቤቱ ያቀረበውን አቤቱታ እንዲቀበል ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጡት ዳኞች፤ ከችሎት ውጪ ለግማሽ ሰዓት ያህል በጉዳዩ ላይ ከተመካከሩ በኋላ ውሳኔያቸውን በግራ ዳኛ በኩል በንባብ አሰምተዋል። ምንም እንኳ ዐቃቤ ህግ ለጠበቆች አስተያየት ምላሹን ያቀረበው ዘግይቶ ቢሆንም፤ ክርክሩን ማጠቃለል ያለበት ዐቃቤ ህግ በመሆኑ ምላሹን ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ እንደተፈቀደለት ገልጸዋል። 

የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡት መከራከሪያ የፍሬ ነገር ብቻ ሳይሆን የህግ ጭምር መሆኑን የጠቀሱት የግራ ዳኛዋ ይህን ለመመርመር ጊዜ እንደሚያስፈልግም አክለዋል። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በቀረቡት መከራከሪያዎች ላይ ብይን ለመስጠት ከአንድ ወር ከ18 ቀን በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቀደመው ችሎት ያቀረበውን አቤቱታ ተመልክቶ ትዕዛዞች አስተላልፏል።

ተከሳሹ የጤና ችግር እንዳለበት የሚያስረዳ የህክምና ማስረጃ ማቅረቡን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፤ ይህን ታሳቢ በማድረግ ከቤተሰቡ በየዕለቱ ምግብ እንዲገባለት ያቀረበው ጥያቄ ባለበት ማረሚያ ቤት ተፈጻሚ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተመሳሳይ ምክንያት ሽፍን ጫማ ማድረግ እንዲፈቀድለት እና መደገፊያ ያለው ወንበር እንዲገባለት ያቀረበውን አቤቱታም፤ ማረሚያ ቤቱ እንደማይቃወም በመግለጹ ጫማው እና ወንበሩ እንዲገባለት ፍርድ ቤቱ አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)