የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ “በሰሜን ኢትዮጵያ ቀውስ ላይ ለመወያየት” ለሶስተኛ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው

ከአንድ ወር በፊት አዲስ አበባ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፤ “በሰሜን ኢትዮጵያ ቀውስ ላይ ለመወያየት” በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው። አምባሳደር ማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙት፤ ሁሉም ወገኖች ውጊያ አቁመው የሰላም ንግግር እንዲያደርጉ የሚያሳስብ መልዕክት ይዘው እንደሆነ የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ  ካሪን ጄን ፒየር ትላንት አርብ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

ካሪን ጄን ፒየር በዚሁ መግለጫቸው “የፕሬዝዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ማይክ ሐመር በሰሜን ኢትዮጵያ ቀውስ ላይ ለመነጋገር ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ይጓዛሉ” ብለዋል። ልዩ ልዑኩ በኢትዮጵያ የሚቆዩት ከነገ እሁድ ነሐሴ 29 ጀምሮ እስከ መስከረም 5፤ 2015 እንደሚሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።  

የአሁኑ የአምባሳደር ሐመር ጉዞ በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ዳግም ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ነው። የአሜሪካው ልዩ ልዑክ በአሁኑ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እና ከአፍሪካ ህብረት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል። ልዩ ልዑኩ የተለያዩ ክልሎችን የሚወክሉ ፖለቲከኞችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችን እንደሚያነጋግሩም ተገልጿል።   

ሐመር ባለፈው ግንቦት ወር የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ለሁለት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ሐመር በመጨረሻው የኢትዮጵያ ቆይታቸው፤ ከአውሮፓ ህብረት አቻቸው አኔት ዌበር፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሃና ቴት እንዲሁም ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የካናዳ እና ጣሊያን አምባሳደሮች እንዲሁም የአሜሪካ “ቻርዥ ደ አፌር” ጋር በመሆን ወደ መቐለ አቅንተው ነበር።

የልዩ ልዑካኑ እና የዲፕሎማቶቹ የመቐለ ጉዞ፤ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር የማበረታታት ዓላማ ያነገበ ነበር። ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲካሄድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ውጊያ በመግባታቸው በዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ የነበረው ተስፋ እውን ሳይሆን ቀርቷል። 

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር እና የአሜሪካ አቻቸው ማይክ ሐመር የተካተቱበት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስብስብ ሐምሌ 26፤ 2014 ወደ መቐለ ተጉዞ ውይይት አድርጎ ነበር | ፎቶ፦ ድምፂ ወያነ

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 18፤ 2014 ዳግም ከተቀሰቀሰ ውጊያ ወዲህ ግን ሐመርም ሆኑ የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም። የዋይት ሐውሷ ቃል አቀባይ በትላንቱ ጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ አምባሳደር ማይክ ሐመርም ሆነ አሜሪካ ህወሓት ከትግራይ ክልል ውጪ እያደረገ የሚገኘውን ማጥቃትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጽመውን የአየር ጥቃት እንደሚያወግዙ ገልጸዋል። ቃል አቃባይዋ “ኤርትራ ወደ ግጭቱ ተመልሳ መግባቷን” በተመሳሳይ መልኩ ኮንነዋል።       

ውጊያው ዳግም ከመቀስቀሱ በፊት ለአምስት ወራት ገቢራዊ ሆኖ በቆየው ለሰብዓዊነት ተኩስ የማቆም ውሳኔ “ተበረታተን ነበር” ያሉት ካሪን ጄን ፒየር፤ በአሁኑ ወጊያ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለወታደራዊ አገልግሎት መያዙ “በጥልቅ አሳስቦናል” ሲሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ለተቀሰቀሰው ግጭት “ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሔ” እንደሌለም በመግለጫቸው ጠቁመዋል። ለተቸገሩ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ይቻል ዘንድ፤ ሁሉም ወገኖች ግጭቱን ከማባባስ መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ይህ ዘገባ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]