በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በመጪው 2015 ዓ.ም. ሶስት አዳዲስ የቴሌቪዥን ቻናሎችን ሊከፍት መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ተናገሩ። ትኩረቱን በህጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ያደረገው አንደኛው የቴሌቪዥን ቻናል፤ በመስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንት የሙከራ ስርጭቱን ይጀምራል ተብሏል።
ብሔራዊ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በስሩ የሚያስተዳድረው ኢቢሲ፤ በአሁኑ ወቅት ሶስት የቴሌቪዥን ቻናሎች አሉት። የመጀመሪያው ቻናል ሙሉ ለሙሉ ለዜና እና ወቅታዊ ዝግጅቶች የተመደበ ሲሆን ሁለተኛው በተለያዩ ቋንቋዎች የሚካሄዱ ስርጭቶችን የሚያስተናግድ ነው። ሶስተኛው ቻናል የመዝናኛ ዜናዎች እና ዝግጅቶች የሚተላለፉበት ነው።
ኢቢሲ በ2015 ከሚከፍታቸው አዳዲስ ቻናሎች ውስጥ “ከሞላ ጎደል የዝግጅት ስራው የተጠናቀቀው”፤ “የህጻናት እና ታዳጊዎች ይዘት በተለየ ሁኔታ የሚስተናገድበት” ቻናል እንደሆነ የኢቢሲ መዝናኛ እና ስፖርት ጣቢያ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ መሳይ ወንድሜነህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “የሙከራ ስርጭታችንን ከመስከረም የመጀመሪያ ሳምንት እንጀምራለን ብለን አቅደንን እየሰራን ነው” ያሉት ማኔጂንግ ኤዲተሩ፤ ቻናሉ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ባሉት ጊዜያት ወደ መደበኛ ስርጭት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የ24 ሰዓት ስርጭት ለሚኖረው ለዚህ የቴሌቪዥን ቻናል የሚሆኑ የመጠባበቂያ ፕሮግራሞች ቀረጻ መጀመሩን የጠቆሙት አቶ መሳይ፤ ቻናሉ የሚጠቀምበት ስቱዲዮ ግንባታም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል። የስቱዲዮ እና የቤት ውጭ ቀረጻዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ ቦታዎች ግንባታዎች በመካሄድ ላይ የሚገኙት፤ ኢቢሲ በአዲስ አበባ ከተማ ሸጎሌ አካባቢ እያስገነባው ባለው ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው።
በቻናሉ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ሁሉ “ብቻችንን ልንሸፍነው አንችልም” የሚሉት የኢቢሲ መዝናኛ እና ስፖርት ጣቢያ ማኔጂንግ ኤዲተር፤ ከተባባሪ አዘጋጆች ጋር የመስራት እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል። በመዝናኛ እና በሌሎችም ዘርፎች ከኢቢሲ ጋር በትብብር የሚሰሩ አዘጋጆችን ያህል፤ ለአዲሱ ቻናል ዝግጅቶችን የሚያቀርቡ ተባባሪዎችን በብዛት የማግኘት ችግር ኮርፖሬሽኑ ሊገጥመው ይችላል ሲሉም አክለዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ፤ ለህጻናት እና ታዳጊዎች የሚሆኑ ይዘቶች ያላቸውን ዝግጅቶች “ፕሮዳክሽን” ኢቢሲ ራሱ ለመስራት ማቀዱን አብራርተዋል።
አዲሱ ቻናል ራሱን ችሎ ገቢ እንዲያመነጭ በማድረግ በኩልም ኮርፖሬሽኑ ተግዳሮት ሊገጥመው እንደሚችል ታሳቢ መደረጉንም አቶ መሳይ አመልክተዋል። ይህን ቻናል በተመለከተ ዓመቱን ሙሉ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን የገለጹት ማኔጂንግ ኤዲተሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ ለቻናሉ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል እና ለእርሱ የሚመደበው በጀት ምንጭን የተመለከቱት ይገኙበታል ብለዋል።
የገቢ ምንጭን በተመለከተ የቴሌቪዥን ቻናሉ ወደፊት ይገጥመዋል ተብሎ ለሚታሰበው ተግዳሮት የኢቢሲ ቦርድ እና አመራር ውሳኔ ማስተላለፋቸውን አቶ መሳይ ተናግረዋል። “[ኢቢሲ] በሌሎች ጣቢያዎች ከሚያገኘው ገቢ ላይ እየደጎመም ቢሆን የህጻናቱን ጣቢያ ለ24 ሰዓት ማስኬድ እንዳለበት ተወስኗል” ሲሉ ኮርፖሬሽኑ ያስቀመጠውን የመፍትሔ አካሄድ አስረድተዋል።
ኢቢሲ ከዚህ ቻናል በተጨማሪ በመጪው ዓመት የሚከፍታቸው ሁለት ቻናሎች፤ በኦሮሚኛ እና በእግሊዝኛ ቋንቋ ስርጭታቸውን የሚያካሄዱ ናቸው። የኢቢሲ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የቋንቋዎች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሁሴን የቋንቋ ቻናሎቹ “ገና በጥናት ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “የአፋን ኦሮሞ እና የእንግሊዝኛ [ቻናሎችን] ለመጀመር ስራዎች እየተሰሩ ነው። ዶክመንቶች እያዘጋጀን፣ የፕሮግራም ፎርማቶች እየተቀረጹ ናቸው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)