ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ “በሽብር ፈጠራ ወንጀል” መጠርጠራቸውን ፖሊስ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

ከትላንት በስቲያ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይን “በሽብር ፈጠራ ወንጀል” እንደጠረጠራቸው የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታወቀ። ጋዜጠኞቹ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ሶስተኛ ዙር ውጊያ እያደረገ የሚገኘውን ህወሓትን በመደገፍም ተወንጅለዋል።

የፌደራል ፖሊስ ውንጀላውን ያቀረበውን ዛሬ አርብ ጷጉሜ 4፤ 2014 ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ባስገባው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ደብዳቤ ነው። ፖሊስ በዚሁ ደብዳቤው “የሽብር ቡድን” ሲል ከጠራው ህወሓት “ከፍተኛ አመራሮች ጋር”፤ ሁለቱ ጋዜጠኞች “በተለያየ መንገድ በመገናኘት እና ተልዕኮ በመቀበል” እንደጠረጠራቸው አመልክቷል። 

አንደኛ ተጠርጣሪ ሆና ችሎት የቀረበችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ “የአማራ ህዝብ መንገድ ከፍቶ ሽብር ቡድኑን ማሳለፍ እንዳለበት እና ሽብር ቡድኑ ወደ መሀል ሀገር ገብቶ ህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል መናድ እንዳለበት ፍላጎቷን ገልጻለች” የሚል ውንጀላ ቀርቦባታል። ሁለተኛው ተጠርጣሪ ጎበዜ ሲሳይ “ ‘ጦርነቱ ሰልችቶናል። ከፈለጉ አራት ኪሎ ሄደው ማጽዳት ይችላሉ’ የሚል ቀስቃሽ እና ሀገሪቱ ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር” የሚያደርግ መልዕክት አሰራጭተሃል በሚል በፖሊስ ተወንጅሏል። 

ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም” የተጠረጠሩበትን ወንጀል “በማሰራጨት ላይ እያሉ በተደረገ ክትትል” በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው የፌደራል ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል። ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 በቁጥጥር ስር በዋሉት መዓዛ እና ጎበዜ ላይ የሚደረገውን የምርመራ ስራ፤ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ አስደግፎ “በተገቢውን ሁኔታ ለማጣራት” የፌደራል ፖሊስ የ14 ቀናት “የምርመራ ማጣሪያ” የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ችሎቱን ጠይቋል።

ጋዜጠኞቹን ወክለው ፍርድ ቤት የተገኙት ጠበቆች በበኩላቸው የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል። ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ ጌታነህ “ወንጀሉ እንዴት እና መቼ እንደተፈጸመ ባልተገለጸበት ሁኔታ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ ብቻ ተጠርጣሪዎችን በእስር ላይ ሊያቆይ የሚችል በቂ ምክንያት አይደለም” ሲሉ ተከራክረዋል።

ሌላኛው ጠበቃ አቶ አዲሱ አልጋውም በተመሳሳይ “የቀረበው ወንጀል አግባብ ስላልሆነ መዝገቡ ተዘግቶ ደንበኞቻችን በዋስ እንዲለቀቁ” ሲሉ ጠይቀዋል። የፌደራል ፖሊስ “ምርመራችንን ገና እየጀመርን ስለሆነ” ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ቢወጡ “ምስክር ያባብሉብናል” በሚል ምክንያት የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ያነሱትን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል።  

ፖሊስ ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች “በአካል በመገኛኘት ስብሰባ ሲያደርጉ ነበር” ሲል ከስሷል። ፖሊስ ይህን እየተናገረ ባለበት ሰዓት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች “በፖሊስ አዲስ የፍሬ ነገር ክርክር ተነስቷል” በሚል ለችሎቱ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል። ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ “ ‘በአካል ተገናኝተው ስብስባ አድርገዋል’ የሚለው፤ የእኛን መከራከሪያ መሰረት አድርገው ያቀረቡት አዲስ ፍሬ ነገር ነው” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።  

ፖሊስ በበኩሉ “ወንጀሉ የተፈጸመው በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ አይደለም። የአማራን ህዝብ ሲሰበስቡ ነበር” ሲል ስብሰባው ተካሄዶባቸዋል ወዳላቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ሄዶ የምስክር ቃል እንደሚቀበል ለችሎቱ አስረድቷል። የጊዜ ቀጠሮ መጠያቂያ ደብዳቤው ላይ ስብሰባ ስለመደረጉ ፖሊስ አለማቅረቡን የጠቀሰው ችሎቱ፤ “ስብሰባ ተደረገ” የሚለውን የፖሊስ መከራከሪያ እንደማይመዘግበው ገልጿል።   

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ እና የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ተመልክቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት ቀጠሮ በመስጠት ከምሳ ሰዓት በፊት የነበረውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ትላንት ሐሙስ ጷጉሜ 3፤ 2014 ፍርድ ቤት ቢቀርቡም፤ የጊዜ ቀጠሮች ችሎቱ በበርካታ መዝገቦች መደራረብ ምክንያት የእነርሱን ጉዳይ ለዛሬ ማስተላለፉ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)