በቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ላይ ክስ ለመመስረት ለዐቃቤ ህግ ሰባት ቀናት ተፈቀደ

በሃሚድ አወል

ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ታስረው ምርመራ ሲደረግባቸው በቆዩት በቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ላይ ክስ ለመመስረት ለዐቃቤ ህግ ሰባት ቀናት ተፈቀደ። “በስልጣን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል” በተጠረጠሩት በቀድሞው ኃላፊ ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜውን የፈቀደው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። 

ችሎቱ ጉዳዩን ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው፤ የፌደራል ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ እንዲያቀርብ ነበር። ዛሬ አርብ ጷጉሜ 4፤ 2014 ከሰዓት በነበረው የችሎት ውሎ፤ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ መላኩን ገልጿል። ይህን ተከትሎ የዶ/ር ሙሉቀን ጠበቆች “ምርመራው የተጠናቀቀ ስለሆነ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ እንዲዘጋልን” ሲሉ ለችሎቱ አመልክተዋል።

ከተጠርጣሪው ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሞላልኝ መለሰ “ደንበኛዬ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። የተጠርጣሪውን ጠበቃ የዋስትና ጥያቄ በተመለከተ “ዐቃቤ ህግ መልስ ይሰጥበት” ሲል ፖሊስ ለችሎቱ መልሷል። ሆኖም ይህ የፖሊስ ምላሽ ከጠበቆች ተቃውሞ ገጥሞታል። 

የዶ/ር ሙሉቀን ሁለተኛ ጠበቃ አቶ አድያም ሰገድ አጥናፉ “በዚህ መዝገብ ክርክር ላይ ዐቃቤ ህግ ከመነሻውም አልነበረም። አስተያየት ሊሰጥበትም አይገባም” ሲሉ መከራከሪያቸውን አስመዝግበዋል። በዛሬው የችሎት ክርክር ላይ ዘግይቶ የተገኘው ዐቃቤ ህግ፤ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደደረሰው በመግለጽ የክስ መመስረቻ 15 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።

ይህን የዐቃቤ ህግን ጥያቄ ተከትሎ ጠበቃ ሞላልኝ በመዝገቡ ላይ ተከራካሪው ፖሊስ መሆኑን ጠቁመው፤ “ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ የመጠየቅ መብት ያለው ፖሊስ ነው” ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። አቶ ሞላልኝ አክለውም “ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ጥያቄ፤ ከምርመራ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪውን በማረፊያ ቤት ለማቆየት አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚገልጽ አይደለም” ሲሉ ተሟግተዋል። 

ጠበቃ አድያም ሰገድ በበኩላቸው፤ ዐቃቤ ህግ ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ያቀረበው ጥያቄ “የህግም፣ የምክንያትም መሰረት ስለሌለው ውድቅ ተደርጎ ተጠርጣሪው የዋስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ነው የምናመለክተው” ብለዋል። ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ ችሎት ፊት የቀረቡት ተጠርጣሪው ዶ/ር ሙሉቀንም ችሎቱ እድል ሰጥቷቸው ተናግረዋል። 

የአዲስ አበባ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ሙሉቀን፤ በዋስ ቢወጡ ግዴታቸውን አክብረው ችሎት ፊት እንደሚቀርቡ በማንሳት የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል። ዶ/ር ሙሉቀን ከስራ በታገዱበት እና ያለመከሰስ መብታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በተነሳበት ዕለት መካከል የነበረውን ቀን በማስታወስ፤ መሸሽ ቢፈልጉ በዚያን ጊዜ ሊሸሹ ይችሉ እንደነበር አስረድተዋል። “ዋስትና ቢሰጠኝ የትም ሀገር አልሄድም” ያሉት ዶ/ር ሙሉቀን “ፍትህ አገኛለሁ” ብለው ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ለችሎቱ ገልጸዋል። 

ለተጠርጣሪ ጠበቆች አስተያየት ምላሽ የሰጠው ዐቃቤ ህግ፤ በተጠርጣሪው እና በጠበቆቻቸው የተነሳውን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል። ዐቃቤ ህግ ለመቃወሚያ ያነሳቸው ምክንያቶች፤ ዶ/ር ሙሉቀን “በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን” እና “ጥፋተኛ ከተባሉ ከአስር ዓመት በላይ እስር ሊፈረድባቸው ይችላል” የሚሉትን ነው። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ ከጠየቀው የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ግማሹን በመቀነስ ሰባት ቀናትን ፈቅዷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)