የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ሰባት ቀናት ፈቀደ

በሃሚድ አወል

“በሽብር ፈጠራ ወንጀል” ተጠርጥረው ከትላንት በስቲያ በቁጥጥር ስር በዋሉት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይ ሰባት የምርመራ ቀናት ተፈቀደ። የምርመራ ቀናቱን የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። 

ችሎቱ በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ የምርመራ ቀናቱን የፈቀደው “ከወንጀሉ አይነት እና ስፋት አንጻር ፖሊስ የሚያሰባስባቸው የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ” እና “የተጀመረውን ምርመራ ሊያጠናክር የሚችል ጊዜ መስጠቱን አምኖበት” መሆኑን ገልጿል። 

ችሎቱ የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ያነሱትን የዋስትና መብት ሳይቀበለው ቀርቷል። በተጨማሪም ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ አልጋው “ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መታየት አለበት” ሲሉ ያቀረቡትን መከራከሪያ ውድቅ አድርጎታል። ችሎቱ መከራከሪያቸውን ውድቅ ያደረገው፤ ፖሊስ “ወንጀሉ በሚዲያ ብቻ የተፈጸመ አይደለም” ማለቱን ተከትሎ ነው። 

የፌደራል ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የተመለከተው ችሎቱ፤ “ሰፊ የምርመራ ጊዜ መስጠት” እንዳላሳመነው በመግለጽ ከተጠየቀው ጊዜ ግማሹን ብቻ ፈቅዷል። መስከረም 6፤ 2015 በሚኖረው ቀጣይ ቀጠሮም፤ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ እንዲያቀርብ ችሎቱ አዝዟል። 

ችሎቱ ትዕዛዙን ካስተላለፈ በኋላ ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ አንደኛ ተጠርጣሪን የተመለከተ አቤቱታ በቃል አቅርበዋል። አቶ አዲሱ “መዓዛ በቁጥጥር ስር ከዋለችበት ቀን ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በምሽት እየተጠራች ቃል ስጪ ተብላለች” ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል። ይህን ተከትሎም ፖሊስ በደንበኛቸው ላይ የሚያደርገውን የምሽት ምርመራ እና ቃል መቀበል እንዲያቆም ማሳሰቢያ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ደንበኛቸው ከዚህ በኋላ ቃሏን መስጠት እንደማትፈልግ በችሎቱ እንዲመዘገብላቸው አመልክተዋል። ከዚህ በኋላ ቃሏን እንደሰጠች ተደርጎ በፖሊስ የሚቀርብን ማስረጃ ችሎቱ እንዳይቀበልም ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል። አቤቱታውን ያደመጠው ችሎቱ፤ ፖሊስ የተጠርጣሪን ቃል በምሽት እንዳይቀበል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)