የአፍሪካ ህብረት የኦሊሴጉን ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኃላፊነት አራዘመ

በትግራይ ተፋላሚ ኃይሎች ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብባቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ በአፍሪካ ህብረት  በኩል የተሰጣቸው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኃላፊነት ተራዘመላቸው። የኦባሳንጆ የልዩ ልዑክ ሹመት መራዘሙን የገለጹት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ናቸው። 

ሊቀመንበሩ ይህን ያሉት ዛሬ ቅዳሜ ጷጉሜ 5፤ 2014 በትዊተር ገጻቸው ባሳፈሩት መልዕክት ነው። ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን በፎቶዎች አስደግፈው የገለጹት ማህማት፤ በእርሳቸው ላይ አሁንም “ሙሉ እምነት እንዳላቸው” አስታውቀዋል።

ከኦባሳንጆ ጋር በነበራቸው ቆይታም፤ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላም እና እርቅ ይመጣ ዘንድ ከሁሉም ወገኖች እና ከዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ጋር እያከናወኗቸው ያሏቸውን ስራዎች እንዲቀጥሉ እንዳበረታቷቸው ማህማት በትዊተር መልዕክታቸው አስፍረዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ እንዲሆኑ የሾሟቸው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ነበር። 

ኦባሳንጆ የልዩ ልዑክ ኃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ጭምር በተደጋጋሚ በመጓዝ የበኩላቸውን ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት “ዘገምተኛ” ቢሆንም በተፈላሚ ወገኖች መካከል የተኩስ ማቆም ስምምነት የመድረስ ተስፋ እንዳለ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። 

የ85 ዓመቱ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ይህን ካስታወቁ በኋላ በተከተሉት ወራት ግን የትግራይ ተፋላሚ ኃይሎች በእርሳቸው የአሸማጋይነት ሚና ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ እና ተቃውሞ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተፈርሞ ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የተሰራጨ ደብዳቤ፤ ኦቦሳንጆ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቅርበት አላቸው በሚል የገለልተኝነት ጥያቄን ማንሳቱ ይታወሳል።

በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በኦባሳንጆ አሸማጋይነት ድርድር ከሚደረግ ይልቅ፤ በወቅቱ በስልጣናቸው ላይ በነበሩት የኬንያው ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ አማካኝነት እንዲደረግ የትግራይ ኃይሎች ፍላጎታቸውን አስታውቀው ነበር። በኬንያ መንግስት አመቻችነት በሚደረገው በዚህ ድርድር ላይም፤ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚፈልጉ የትግራይ ኃይሎች በሰኔው ደብዳቤያቸው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)