የትግራይ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር ለሚደረገው ድርድር፤ የቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የሚገኙበት ቡድንን መወከሉን አስታወቀ። ለዚህም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በሁሉም ወገን ከስምምነት ላይ የሚደረስበትን የግጭት ማቆምን ወዲያውኑ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጿል።
የትግራይ ክልል መንግስት ይህን ያስታወቀው የውጭ ጉዳይን በሚከታተለው ጽህፈት ቤቱ በኩል ዛሬ መስከረም 1፤ 2015 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። የክልሉ መንግስት በዛሬው መግለጫው “አሳዛኝ” ሲል ለጠራው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚቻለው “በሰላማዊ ንግግር ብቻ እንደሆነ እናምናለን” ብሏል።
የክልሉ መንግስት በዛሬው መግለጫው ከግጭት ማቆም ሂደት በኋላ ቀጣዩ እርምጃ “በሁሉን አቀፍ ድርድር የተኩስ አቁም” ማድረግ መሆኑን ጠቅሷል። ይህንን ተከትሎ ደግሞ “አሁን ላለው ግጭት መንስኤ የሆኑትን ጉዳዮች ለመፍታት ሁሉን ያሳተፈ የፖለቲካ ውይይት ማካሄድ” እንደሚገባ ጠቁሟል። ይህን ድርድር እውን ለማድረግ “ያለምንም መዘግየት የሚሰማራ የድርድር ቡድን” ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።
ወደፊት በሚካሄዱ ድርድሮች የትግራይ ክልል መንግስትን በሚወክለው ቡድን ውስጥ ከተካተቱት ተደራዳሪዎች ውስጥ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚገኙበት በዛሬው መግለጫ ይፋ ተደርጓል። ሌተናል ጄነራል ጻድቃን የትግራይ ኃይሎች ላለፉት 23 ወራት ከፌደራል መንግስቱ ጋር ጦርነት እያካሄዱ የሚገኙትን የትግራይ ተዋጊ ኃይሎች ከሚመሩ ወታደራዊ አዛዦች መካከል ስማቸው በጉልህ የሚነሳ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ የሆነው ህወሓት እና የትግራይ ማዕከላዊ ዕዝ የተባለው ወታደራዊ ክፍል ቃል አቃባይ በመሆን የትግራይ ተዋጊ ኃይሎችን አቋም ለመላው ዓለም ሲያስታውቁ የቆዩ ናቸው። የትግራይ አማጽያን ለድርድር የወከሏቸውን ግለሰቦች ማንነት ይፋ ያደረጉት ከፌደራል መንግስቱ ሁለት ወር ገደማ ዘግይተው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የሰላም አማራጭ ኮሚቴ” ያሉትን ቡድን ማዋቀራቸውን ያስታወቁት ሰኔ 20፤ 2014 ነበር። ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለሚደረገው ድርድር የፌደራል መንግስትን የሚወክለው ይህ ቡድን የሚመራው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ሰባት አባላት ባሉት በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዮስ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተካትተዋል።
ቡድኑ በተጠናቀቀው 2014 ዓመት መጨረሻ ላይ ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊያመጣ የሚችል የሰላም ምክረ ሀሳብ ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጎ ነበር። በትግራይ አማጽያን እና በፌደራሉ መንግስት ኃይሎች መካከል ሶስተኛ ዙር ውጊያ የተቀሰቀሰው ይህ የሰላም ምክረ ሀሳብ መዘጋጀቱ ይፋ ከተደረገ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር።
ለአምስት ወራት ገደማ ጋብ ብሎ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ነሐሴ 18፤ 2014 ዳግም ማገርሸቱ ከተሰማ በኋላ በኢትዮጵያ ተፈላሚ ወገኖች መካከል ድርድር እንዲካሄድ ዋነኛውን ጥረት ሲያደርግ በቆየው በአፍሪካ ህብረት፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ውግዘት ገጥሞታል። የትግራይ ክልል መንግስት በአፍሪካ ህብረት በሚመራ የሰላም ሂደት ላይ ቅሬታዎችን ሲያቀርብ ቢቆይም በዛሬው መግለጫው ግን በህብረቱ ጥላ ስር በሚደረግ የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም ሂደት “እምነት የሚጣልበት ይሆናል” ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጿል። የሰላም ድርድሩ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ያላቸውን አሸማጋዮች ማካተት እንዳለበትም ጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪ የሁለቱን ወገኖች የጋራ መተማመን የሚያጎለብቱ፣ በሰላም ሂደቱ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳድጉ እና ቃል ኪዳኖች መተግበራቸውን የሚቆጣጠሩ አለም አቀፍ ታዛቢዎችም የሂደቱ አካል መሆን እንዳለባቸው መግለጫው አመልክቷል።
ከአሸማጋዮች እና ከታዛቢዎች በተጨማሪ የሰላም ሂደቱን ሐቀኝነት በተመለከተ አስፈላጊ መመሪያ እና ምክር የሚለግሱ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችም እንዲሁ በሂደቱ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው የትግራይ ክልል መንግስት አቋሙን አሳውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)