የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ ለማቆም እንዲሰሩ እና የፊት ለፊት ንግግር እንዲያካሄዱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ጥሪ አቀረቡ። የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ዛሬ እሁድ ምሽት ባወጡት መግለጫ፤ የትግራይ ክልል መንግስት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና በአፍሪካ ህብረት በሚመራ የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ፍቃደኝነት ማሳየቱን በበጎ መቀበላቸውን አስታውቀዋል።
ሙሳ ፋኪ ማህማት በዛሬው መግለጫቸው፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚደረገው ድርድር የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል መንግስት የሚስማሙባቸው “ዓለም አቀፍ አጋሮችን” እንደሚያካትት ጠቁመዋል። የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ትላንት ቅዳሜ ከአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ማይክ ሐመር ጋር በተገናኙበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እልባት ለመስጠት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በተፋላሚ ወገኖች መካከል ለሚደረገው ድርድር “የዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ አስፈላጊነት ላይ ተሰማምተናል” ብለው ነበር።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ይህን መግለጫ ያወጡት፤ የትግራይ ክልል መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ባስታወቀ በሰዓታት ልዩነት ነው። የትግራይ ክልል መንግስት በዚሁ መግለጫው በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረግ የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
የክልሉን መንግስት መግለጫ በበጎ እንደሚቀበሉት የገለጹት የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር፤ ይህ አዎንታዊ እርምጃ በኢትዮጵያ የታጣውን ሰላምን ወደነበረበት ለመመለስ “ልዩ አጋጣሚ ነው” ብለዋል። በዚህ ረገድ የትግራይ ክልል መንግስት በድርድር ለመሳተፍ ዝግጁነቱን መግለጹን ሙሳ ፋኪ ማህማት አድንቀዋል። የክልሉ መንግስት ውሳኔ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት ከቀረበው ተመሳሳይ ጥሪ ጋር የተስማማ መሆኑን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
ማህማት በዚሁ መግለጫቸው፤ የአፍሪካ ህብረት ለጠንካራ እና ተአማኒ የሆነ ሰላማዊ ሂደት ያለውን ለረጅም ጊዜ የቆየ እና አሁንም የዘለቀ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ መቀስቀሱን ተከትሎ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሲያሳስብ የቆየው የአፍሪካ ህብረት፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ እና መፍትሔ የሚያፈላልጉ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በመሾም በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
የህብረቱን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኃላፊነት የተረከቡት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ጭምር በተደጋጋሚ በመጓዝ በተፈላሚ ወገኖች መካከል ድርድር እንዲጀመር ግፊት ሲያደርጉ ነበር። ልዩ ልዑኩ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ቀረቤታ አላቸው” የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ የነበሩት የትግራይ ኃይሎች፤ በአፍሪካ ህብረት ከሚመራው የሰላም ሂደት ይልቅ በኬንያ ለሚደረግ ድርድር ቅድሚያ እንደሚሰጡ አስታውቀው ነበር።
የትግራይ ክልል መንግስት የውጭ ጉዳይን በሚከታተለው ጽህፈት ቤቱ በኩል ዛሬ ያወጣው መግለጫ ግን ይህንን አቋሙን የቀየረ ነው። ይህን መግለጫ ተከትሎ የወጣው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መልዕክት፤ በውጊያው ተሳታፊ በሆኑት ሁለቱም ወገኖች የታየው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የሚመሰገን ነው ብለዋል። ይህ ቁርጠኝነት፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያንን የሰላም፣ የመረጋጋት እና የዘላቂ ልማት ህልም እና ታላቅ ጥቅም ለማሳካት ሊጠቅም እንደሚገባ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)