ኤርትራ እና ሌሎች አካላት የሰሜን ኢትዮጵያውን ግጭት “ከማቀጣጠል እንዲቆጠቡ” የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አሳሰቡ። ዓለም አቀፍ አጋሮች ግጭቱን በሰላም ለመፍታት የሚደረገውን ሂደት ለመደገፍ ዝግጁ እንዲሆኑም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አንቶኒ ብሊንከን ማሳሰቢያውን እና ጥሪውን ያቀረቡት የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት በማስመልከት ዛሬ እሁድ መስከረም 1፤ 2015 እኩለ ሌሊት ገደማ ባወጡት መግለጫ ነው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዛሬ ባወጣው መግለጫ ውጊያ ለማቆም እና ያልተፈቱ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁን “እናበረታታለን” ብለዋል።
የትግራይ ክልል መንግስት ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረግ የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጎ ነበር።
የክልሉን መንግስት መግለጫ ተከትሎ የወጣው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ፤ በኢትዮጵያ በመካሄድ ያለው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በአፋጣኝ ወደ ንግግር እንዲመጡ የአፍሪካ ህብረት እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቋል።
ብሊንከን በዛሬው መግለጫቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ሲል ከትግራይ ኃይሎች ጋር “በየትኛውም ስፍራ፣ በማንኛውም ጊዜ” ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መግለጹን አስታውሰው፤ ለዚህ የመንግስት ዝግጁነት የሚሰጥ ምላሽን ሀገራቸው እንደምታበረታታ አመልክተዋል። የአዲስ አመት መንፈስን ታሳቢ በማድረግ፤ የኢትዮጵያ መሪዎች ሀገሪቱን መከራ ወደሚያበቃበት እና ዘላቂ ሰላም ለማጎናጸፍ ወደሚያስችል መንገድ እንደሚሯት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንደምትደግፍ የጠቆሙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ ከሀገሪቱ ጋር ወደነበራት “ጠንካራ አጋርነት” መመለስ እንደምትሻ በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)