የኢትዮጵያ ተፈላሚ ወገኖች በግንኙነታቸው ላይ መተማመን እንዲገነቡ ኢጋድ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እና በትግራይ ክልል ያሉ ባለስልጣናት ያልተፈቱ ጉዳዮችን ለመፍታት በግንኙነታቸው ላይ መተማመን እንዲገነቡ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጥሪ አቀረቡ። ሁለቱ ወገኖች ለሰላም ያሳዩአቸውን ጥረቶች በትዕግስት እና በጠንካራ ቁርጠኝነት እንዲቀጥሉበትም ዋና ጸሀፊው አሳስበዋል። 

ዶ/ር ወርቅነህ ዛሬ ሰኞ መስከረም 2፤ 2014 ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመመለስ ጠንካራ ፈቃደኝነት በማሳየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲደረግ ተፋላሚ ወገኖች ፍቃደኝነታቸውን የገለጹበት ይህ ድርድር፤ ኢጋድ በጉዳዩ ላይ ከያዘው አቋም ጋር የተስማማ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ኢጋድ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ በጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው፤ የዲፕሎማሲ አካሄድ ነው ባይ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት፤ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ቅሬታዎችን በውይይት እና ሁሉን አካታች በሆነ የፖለቲካ ሂደት ለመፍታት አለው ያሉትን “ያልተቋረጠ ቁርጠኝነት” የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ በመግለጫቸው በአዎንታዊነት አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ወገኖች ይህን አጋጣሚ እንዲጠቀሙም ተማጽነዋል። የትግራይ ክልል መንግስት በትላንትናው ዕለት ለውይይት ዝግጁ መሆኑን በማስመልከት ያወጣው መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ መንግስት ሲቀርቡ ከነበሩት ተመሳሳይ ጥሪዎች ጋር የተስማማ መሆኑን ዶ/ር ወርቅነህ ጠቅሰዋል። የክልሉ መግለጫ የሚያበረታታ መሆኑንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)