በምስረታ ላይ የነበረው የዳሞታ ባንክ ፈረሰ

በሃሚድ አወል

“ዳሞታ” በሚል ስያሜ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የምስረታ አክሲዮኖች ሽያጭ ሲያከናውን የቆየው ባንክ፤ የማደራጀት ሂደቱ ተቋርጦ መፍረሱን የአደራጅ ኮሚቴው እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቁ። ባንኩ የምስረታ ሂደቱን ያቋረጠው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የሚጠበቅበትን የመነሻ ካፒታል ከባለ አክሲዮኖች መሰብሰብ ባለመቻሉ ነው ተብሏል።

የዳሞታ ባንክ የአክሲዮን ማህበር በማቋቋም የአዲስ ባንክ ምስረታ እንቅስቃሴውን የጀመረው በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ነበር። የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ በወቅቱ ለብሔራዊ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ፤ የፋይናንስ ተቋሙን ለማደራጀት የሚያስችሉ ዝግ የባንክ ሂሳቦችን ለመክፈት ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት አግኝቷል።

የዳሞታ ባንክ በወቅቱ በስራ ላይ በነበሩ 17 ባንኮች የአክሲዮን ሽያጭ ሲጀመር የአንድ አክሲዮን ዋጋን በ1,000 ሺህ በመተመን ነበር። ባንኩ በመጀመሪያ ለሽያጭ ያቀረበው ዝቅተኛ የአክሲዮን መጠን 50 ሺህ ብር የነበረ ቢሆንም፤ ከአራት በኋላ ግን ተመኑን ወደ 10 ሺህ ዝቅ አድርጎት ነበር። 

አንድ ባንክ ለማቋቋም በወቅቱ በብሔራዊ ባንክ በመስፈርትነት ይጠየቅ የነበረው የገንዘብ መጠን 500 ሚሊዮን ብር ነበር። የዳሞታ ባንክ ምስረታን አስመልክተው በጥር 2013 ላይ መግለጫ የሰጡት የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኤሊያስ ሎሃ፤ በመስፈርትነት የሚጠየቀውን ገንዘብ “በአጭር ጊዜ ለማሰባሰብ በቂ ደንበኛ አለን ብለን እናስባለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር። 

በምስረታ ላይ የነበረው ባንክ የተፈረመ 370 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዳለውም አቶ ኤሊያስ በጋዜጣዊ መግለጫው ጠቁመዋል። የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ይህን በተናገሩ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ግን  አዲስ ባንክ ለመመስረት የሚያስፈልገውን የመመስረቻ ካፒታል የቀየረ መመሪያ ጸድቆ ተግባራዊ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያዚያ 2013 ዓ.ም ያጸደቀው መመሪያ፤ አዲስ የሚመሰረቱ ባንኮች መሰብሰብ የሚጠበቅባቸውን የተከፈለ ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ያሳደገ ሆኗል። ይህ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በወጣበት ጊዜ ዳሞታ ባንክን ጨምሮ 20 ባንኮች በምስረታ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ አምስት ባንኮች ደግሞ ወደ ስራ ለመግባት የብሔራዊ ባንክን የፍቃድ ማረጋገጫ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።

የወቅቱ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በምስረታ ላይ የነበሩ ባንኮች በስድስት ወራት ጊዜ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንዲኖራቸው ግዴታ ጥሏል። ባንኮቹ ከተመሰረቱ በኋላ የተከፈለ ካፒታላቸውን በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያሳድጉም መመሪያው የጊዜ ገደብ አስቀምጧል። ሆኖም በምስረታ ላይ ከነበሩ ባንኮች ከሁለቱ በስተቀር ሁሉም ባንኮች በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተቀመጠላቸውን መስፈርት መሟላት ሳይችሉ ቀርተዋል። 

ከዚህ መመሪያ መውጣት በኋላ የዳሞታ ባንክ የምስረታ ሂደቱን ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ቀጥሎ የነበረ ቢሆንም፤ አደራጆቹ ባቀረቡት ጥያቄ  ሂደቱ ካለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ ተቋርጦ፤ ባንኩ “በመፍረስ ላይ ያለ” መሆኑን  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ብሔራዊ ባንክ ይህን ያስታወቀው ዝግ የባንክ ሂሳብ ከፍተው የዳሞታ ባንክ አክሲዮኖችን ሲሸጡ ለነበሩ 17 ባንኮች የዛሬ ሁለት ሳምንት በፊት በጻፈው ደብዳቤ ነው። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚሁ ደብዳቤው፤ ባንኩን ለመመስረት “የተሰበሰበው ገንዘብ ለባለአክሲዮኖች ለመመለስ እንዲቻል” በባንኮቹ የዝግ ሂሳቦች የተቀመጠው ገንዘብ እንዲለቀቅ በአደራጆች ጥያቄ መቅረቡን አስፍሯል። በጥያቄው መሰረት ለባንኩ ባለ አክሲዮኖች ገንዘብ እንዲመለስ መወሰኑን በደብዳቤው ገልጿል። አስራ ሰባቱ ባንኮች ገንዘብ ላስቀመጡ ባለ አክሲዮኖች ክፍያ እንዲፈጽሙም ብሔራዊ ባንክ በዚሁ ደብዳቤው አሳስቧል። 

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዳሞታ ባንክ አደራጅ ኮሚቴ አባል፤ “ለህዝቡ ገንዘቡ እንዲመለስ ተደርጓል” ሲሉ የምስረታ ሂደቱ መቆሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ግለሰቡ ሂደቱ ስለተቋረጠበት ምክንያት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

ጉዳዩን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ ግን የዳሞታ ባንክ የማደራጀት ሂደት የተቋረጠው “ከካፒታል ጋር በተያያዘ” ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ለባንኩ መፍረስ ምክንያት ነው የተባለውን የካፒታል ማሰብሰብ ጉዳይ በተመለከተ ከባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኤሊያስ ሎሃ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። 

የዳሞታ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ ለማከናወን በአዲስ አበባ እና ወላይታ ሶዶ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ባንኩ በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ለፕሮጀክት ጽህፈት ቤትነት ሲጠቀምበት የነበረው ቢሮ፤ በአሁኑ ወቅት በሌላ ድርጅት መያዙን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በስፍራው በመገኘት አረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ አግኝተው በስራ ላይ የሚገኙ ባንኮች ብዛት 30 ደርሷል። አማራ፣ ፀሐይ እና አሐዱ ባንኮች በተጠናቀቀው 2014 ዓ.ም ሁለተኛ አጋማሽ ወደ ስራ የገቡ የግል ባንኮች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)