የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ከአንድ ወር በኋላ አባላቱን በድጋሚ ለስብሰባ ጠራ

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ከነገ በስቲያ ቅዳሜ መስከረም 7፤ 2015 ለሚያካሄደው ጉባኤ ለአባላቱ ጥሪ አደረገ። የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አርሽያ አህመድ የምክር ቤቱ ጉባኤ መጠራቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባላት፤ በቅዳሜው ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደደረሳቸው ገልጸዋል። የዞኑ ምክር ቤት የደቡብ ክልልን ለሁለት በሚከፍለው የ“ክላስተር” አደረጃጃት ላይ ለመወያየት ባለፈው ነሐሴ ወር ከጠራው አስቸኳይ ጉባኤ ወዲህ ለስብሰባ ሲቀመጥ የቅዳሜው የመጀመሪያው ይሆናል። 

ምክር ቤቱ ከአንድ ወር በፊት ነሐሴ 5፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ የጉራጌ ዞንን ከሌሎች የደቡብ ክልል አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር በማዳመር የጋራ ክልል ለመመስረት የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። ሶስቱ የዞኑ ምክር ቤት አባላት፤ የቅዳሜው ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳ የ2014 ዓመት በጀት አፈጻጸም ሪፖርትን ማድመጥ እና የ2015ን በጀት ማጽደቅ ሊሆን እንደሚችል ቢገምቱም፤ የ“ክላስተር” አደረጃጀት ጉዳይ ግን በድጋሚ ሊነሳ ይችላል ይላሉ።  

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዞኑ የምክር ቤት አባል “የክላስተርን ጉዳይ ሊያመጡት ይችላሉ ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ክላስተሩ ያለቀለት ጉዳይ ነው” የሚሉት ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ “አጀንዳ አይሆንም፤ አያነሱትም ብለን አናስብም” ሲሉ ተመሳሳይ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 

ሶስተኛው የዞኑ ምክር ቤት አባል ግን የጉባኤው አጀንዳ ካለፈው ዓመት “ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና  በጀት ማጽደቅ” የዘለለ አይሆንም ባይ ናቸው። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት እስካሁን ድረስ የ2014 በጀት ዓመትን አፈጻጸም ግምገማ አላከናወነም፤ ለ2015 የሚሆን በጀትም አላጸደቀም። 

ሶስቱም የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባላት፤ ከነገ በስቲያ የሚካሄደው ጉባኤ “መደበኛ” ይሁን አሊያም “አስቸኳይ” እንደማያውቁ ገልጸዋል። የዞኑ ምክር ቤት በተለምዶ በአንድ አመት ውስጥ አራት መደበኛ ጉባኤዎችን እንደሚያካሄድ የጠቀሱት አንድ የምክር ቤት አባል፤ ይሄኛው ወቅት ግን መደበኛ ጉባኤ የሚጠራበት አይደለም ይላሉ። 

የቅዳሜው ጉባኤን አይነት እና ለስብሰባው የተያዘውን አጀንዳ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አርሽያ አህመድ፤ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል። የጉራጌ ዞን በደቡብ ክልል ከሚገኙ መዋቅሮች ውስጥ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ባለማጽደቅ ብቸኛው ነው።   

የዞኑ ምክር ቤት “ክላስተር” አደረጃጃት ውድቅ ካደረገ ቀናት በኋላ የፌደሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ክልል የሚመሰረት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወስኗል። ጉራጌ ዞንን ጨምሮ አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ የሚገኙበት ክፍልን ደግሞ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ እንዲቀጥሉ ውሳኔ አስተላልፏል። 

ነሐሴ 12፤ 2014 በተካሄደው በዚሁ የፌደሬሽን ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ “በአንድ ዞን አካባቢ የተፈጠረ ችግር አለ። ጥያቄውን በደንብ ተረድቶ በአግባቡ ውሳኔ ማስወሰን ላይ የተፈጠረ ክፍተት አለ” ሲሉ ተደምጠው ነበር። 

“የተለያዩ የውጭ ጫናዎች ነበሩ። ውጤቱ በሚጠበቀው ልክ አልሆነም” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በስም ካልጠሩት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ጉባኤ ውሳኔ ጀርባ የነበረውን ምክንያት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አስረድተዋል። አቶ ርስቱ በወቅቱ የነበረውን ንግግራቸውን ያገባደዱት “ቀሪ ተግባቦት ባልተፈጠረባቸው አካባቢዎች፤ ወደ ፊት ቀሪ ስራዎችን እንሰራለን” የሚል ቃል በመግባት ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)