ኡሁሩ ኬንያታ ለሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት “የሰላም ልዩ ልዑክ” ሆነው መሾማቸውን አሜሪካ አደነቀች

በሰሜን ኢትዮጵያ እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊንክ ኮንጎ እየተካሄዱ ላሉ ግጭቶች የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ “የሰላም ልዩ ልዑክ” ሆነው መሾማቸውን አሜሪካ አደነቀች። ኡሁሩ በሰላም ልዩ ልዑክነት የተሾሙበት ወቅት “ለሁለቱም ግጭቶች ወሳኝ በሆነ ጊዜ” መሆኑን በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ገልጿል። 

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ረዳት ሚኒስትር በሆኑት ሞሊ ፊ የሚመራው የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ፤ ለኡሁሩ ኬንያታ ሹመት ድጋፉን የገለጸው ትላንት ሐሙስ ለሊት በይፋዊ የትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት ነው። ቢሮው በዚሁ መልዕክቱ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ስራ “ከፍተኛ ጠቀሜታ” ያለው እንደሚሆን ተስፋውን ገልጿል። 

ኡሁሩ ሹመቱ እንደተሰጣቸው ይፋ የሆነው፤ ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 3፤ 2015 ለአዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣናቸውን በይፋ ካስረከቡ በኋላ ነው። ሩቶ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያ እና የታላላቅ ኃይቆች ቀጠናን ጨምሮ በአካባቢያችን የሚካሄዱ የሰላም ጥረቶችን የኬንያን ሕዝብ ወክለው መምራታቸውን እንዲቀጥሉ ታላቅ ወንድሜ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጠይቄያቸው በደስታ ተቀብለዋል” ሲሉ ተናግረዋል። 

አምስተኛው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው የስልጣን መንበሩን የተረከቡት ሩቶ በዚሁ ንግግራቸው “የኬንያ መንግስት በተለይም እኔ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትን እነዚህን ጥረቶች እንደግፋለን” ሲሉም  ቃል ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በሩቶ የበዓለ ሲመት ስነ ስርዓት ላይ የታደሙት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ውጊያ በተመለከተ ውይይቶች ማካሄዳቸው ተገልጿል። 

ለሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የአፍሪካ ቀን ልዩ ልዑክ ጭምር በመሾም እንቅስቃሴዎች ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ፤ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ ጋር በቅርበት ስትሰራ ቆይታለች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባለፈው ዓመት ህዳር ውስጥ ወደ ኬንያ በተጓዙበት ወቅት በወቅቱ ስልጣን ላይ ከነበሩት አሁሩ ኬንያታ ጋር በአካል ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አንዱ ነበር። 

ኡሁሩ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳይ ከተለያዩ ወገኖች ጋርም ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይተዋል። የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው መንግስት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚካሄድ የሰላም ሂደት ዝግጁ መሆኑን  ባለፈው መስከረም 1፤ 2015 ከማረጋገጡ በፊት፤ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት ለአደራዳሪነት በቀዳሚነት የመረጣቸው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)