ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በታሰሩ ኃላፊዎች ላይ ክስ የሚመሰረትበት ጊዜ በአምስት ቀናት ተራዘመ

በሃሚድ አወል

ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ታስረው ምርመራ ሲደረግባቸው በቆዩት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ እና ሌሎች ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት ተጨማሪ አምስት ቀናት ተፈቀደ። የክስ መመስረቻ ጊዜውን ያራዘመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። 

ችሎቱ ለሁለተኛ ጊዜ የክስ መመስረቻ ጊዜውን የፈቀደው፤ ዐቃቤ ህግ “በሰነዶች ብዛት” ምክንያት ክስ ለመመስረት አለመቻሉን ገልጾ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጡት ከጠየቀ በኋላ ነው። ዐቃቤ ህግ ዛሬ አርብ መስከረም 6፤ 2014 በዋለው ችሎት ተጨማሪ ቀናትን የጠየቀው፤ ማስረጃዎችን ማስተንተን እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ነው። 

ይህንን የፖሊስ ጥያቄ የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ሞላልኝ መለሰ ተቃውመውታል። ባለፈው ሳምንት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ፤ ዐቃቤ ህግ ክስ ለመመስረት ያስችለው ዘንድ ሰባት ቀናት እንደተፈቀዱለት ያስታወሱት ጠበቃው፤ ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ ቀናት ሊፈቀድለት አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። ችሎቱ የዐቃቤ ህግን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲያስከብርላቸው ጠበቃው ጠይቀዋል። 

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ “ዋስትናን በተመለከተ ግልጽ የህግ ክልከላ አለ” ሲል የተጠርጣሪው ጠበቃ ያነሱትን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል። ተጠርጣሪው በወንጀሉ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከአስር ዓመት በላይ እስራት ሊፈረድባቸው እንደሚችል ፤ በዚህም ምክንያት ለተጠርጣሪው ዋስትና ሊፈቅድላቸው አይገባም ብሏል። 

የክስ መመስረቻ ጊዜን በተመለከተ ለችሎቱ ማብራሪያ የሰጠው ዐቃቤ ህግ፤ የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ከደረሰው በኋላ ሊፈቅድለት ይገባ የነበረው 15 ቀናት እንደነበር ጠቁሟል። “እየጠየቅን ያለነው ያልተጠቀምንበት ቀን እንዲሰጠን ነው” ሲልም አክሏል። ዐቃቤ ህግ ባለፈው ሳምንት አርብ ጷጉሜ 4፤ 2014 በነበረው የችሎት ወሎ ለክስ መመስረቻ 15 ቀን ቢጠይቅም፤ በፍርድ ቤት የተፈቀዱለት ሰባት ቀናት ብቻ ነበሩ። 

በዛሬው ችሎት ውሎ የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ በተጠርጣሪው ክስ ለመመስረት ያስችለው ዘንድ ለዐቃቤ ህግ ተጨማሪ አምስት ቀናትን ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ የዶ/ር ሙሉቀንን አቆያየት በተመለከተም “ቀደም ብሎ ትዕዛዝ ስለተሰጠበት” በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ፤ በተጠርጣሪው ጠበቃ በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ከኮንዶሚኒየም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር በዋሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይም ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፏል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የአዲስ አበባ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ አብርሃም ሰርሞሎ ይገኙበታል።  

የቢሮው ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ሙሉቀንን ጨምሮ ሁሉም ግለሰቦች የተጠረጠሩት “ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” በሚል ነው። ከሁለት ወራት በፊት በሐምሌ 2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር በዋሉት በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ሲያከናውን የቆየውን ምርመራ በማጠናቀቁ መዝገባቸው ለዐቃቤ ህግ መሸጋገሩ ከዚህ ቀደም በነበረ የችሎት ውሎ ላይ ተገልጾ ነበር። 

የፌደራል ዐቃቤ ህግ አቶ አብርሃም ሰርሞሎን ጨምሮ በአምስት ተጠርጣሪዎች ላይ ሊመሰርተው ላቀደው ክስ 10 ቀናት በፍርድ ቤት ተፈቅዶለት የነበረ ቢሆንም፤ በዛሬው የችሎት ውሎ ተጨማሪ ቀናትን ጠይቋል። የዐቃቤ ህግን ጥያቄ የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ለክስ መመስረቻ የሚሆኑ አምስት ተጨማሪ ቀናትን ለዐቃቤ ህግ ፈቅዷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)