ኢሠፓን ዳግም ለማቋቋም የተሰባሰቡ አደራጆች፤ የስያሜ ለውጥ በማድረግ ለምርጫ ቦርድ በድጋሚ ማመልከቻ አስገቡ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲን ከ30 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ለመመለስ የተሰባሰቡ አደራጆች፤ የፓርቲውን መጠሪያ ወደ “የኢትዮጵያ ሌበር ፓርቲ” በመቀየር ለምርጫ ቦርድ በድጋሚ ማመልከቻ ማስገባታቸውን አስታወቁ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን አደራጆች ማመልከቻ ባለፈው ሳምንት አርብ መቀበሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። 

በደርግ ዘመነ መንግስት ገዢ ፓርቲ የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ዳግም ለማቋቋም የተሰባሰቡ አደራጆች፤ ለምርጫ ቦርድ የመጀመሪያ ማመልከቻቸውን ያስገቡት ከሶስት ወር በፊት በግንቦት 2014 መጨረሻ ላይ ነበር። አደራጆቹ ያቀረቡትን የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ጊዜያዊ የምዝገባ ፍቃድ ጥያቄ የመረመረው ቦርዱ፤ ማመልከቻቸውን ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ባሳለፈው ውሳኔ ውድቅ አድርጓል።

ምርጫ ቦርድ ማመልከቻውን ካልተቀበለባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ ሊመሰረት የታሰበው ፓርቲ “ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መስክ ህልው ከነበረ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ተመሳሳይ ስያሜ ያለው ነው” በሚል ነው። ኢሠፓ የተባለው ድርጅት እስካሁንም ጸንቶ ባለ አዋጅ እንዲፈርስ መደረጉ፤ ሌላኛው በምርጫ ቦርድ የቀረበው ምክንያት ነበር።

ይህን የቦርዱን ውሳኔ ተከትሎ የፓርቲው አደራጆች “ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንውስደው ወይስ የስያሜ ለውጥ እናድርግ” በሚለው ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የፓርቲው አደራጅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፤ ከፓርቲ ምዝገባ ጋር በተያያዘ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል“ውሳኔው በጽሁፍ ከደረሰው ቀን ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ አቤቱታውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።

የፓርቲው አደራጆች ከፍርድ ቤት ሂደት ይልቅ የስያሜ ለውጥ አማራጭን መከተል እንደመረጡ እኚሁ አደራጅ ገልጸዋል። “ወደ ፍርድ ቤት ብንሄድ የማሸነፍ እድላችን ዝቅተኛ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ጊዜ ይጠፋብናል። ፍርድ ቤት ሄደን ውሳኔ ከማግኘታችን በፊት ሁለት፣ ሶስት ዓመት ሊፈጅ ይችላል” ሲሉ ጉዳዩን ወደ ህግ አካል ለመውሰድ ያልመረጡበትን ምክንያት አብራርተዋል።

አደራጆቹ በስተመጨረሻ የተስማሙበትን ውሳኔ በተመለከተ “ስሙን እነሱ ባሉት መንገድ ትንሽ ‘ሞዲፋይ’ አድርገን፤ ኢሠፓነቱንም ሳይለቅ እንግባ የሚለው ተወሰነ” ሲሉ በስያሜ ለውጡ የነበረውን ሂደት አስረድተዋል። ምርጫ ቦርድ ኢሠፓን ለመመስረት ማመልከቻ ላስገቡ አስተባባሪዎች ከአንድ ወር በፊት በጻፈው ደብዳቤ፤ “በሌላ ስያሜ አላማቸውን ለማራመድ ፓርቲ የማደራጀት እና በህጉ መሰረት ሲመዘገብም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማድረግ” መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን አመልክቶ ነበር።

በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ምክንያት “የኢትዮጵያ ሌበር ፓርቲ” የሚል ስያሜ እንዲይዝ የተደረገው አዲሱ ፓርቲ፤ ቀደም ሲል የተዘጋጀውን ፕሮግራም እና ርዕዮተ ዓለም ይዞ እንደሚቀጥል “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሁለት የፓርቲው አደራጆች ገልጸዋል። አዲሱ ፓርቲ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ወደ “ሊበራሊዝም” ያጋደለ እንደሚሆን ከፓርቲው አደራጆች መካከል አንዱ ከዚህ ቀደም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። 

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ የፓርቲ አደራጅ በበኩላቸው፤ አዲስ የሚቋቋመው ፓርቲ “ዋና ትኩረቱ የሰራተኛውን መብት ማስከበር ነው” ብለዋል። ኢሠፓ በመስከረም 1977 ዓ.ም. ሲመሰረት ያጸደቀው ፕሮግራም “በማርክሲዝም ሌኒኒዝም መሠረተ ሐሳቦች ላይ በመመርኮዝ፣ ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግና ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቱን በማጠናቀቅ ለሶሻሊዝም ምስረታ የቀየሳቸውን ግቦችና የአፈጻጸም ትልሞችን በግልጽ የሚያሳይ” እንደሆነ አስፍሮ ነበር።

በኢትዮጵያ የሰራተኛው መደብ መብቱን ለማስጠበቅ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ትግል ቢያካሄድም፤ “የሠርቶ አደሩን ህዝብ ግንባር ቀደም ፓርቲ” በማስገኘት ረገድ ውጤት የታየው ግን በየካቲት 1966 ዓ.ም. ከፈነዳው አብዮት በኋላ መሆኑን የኢሠፓ ፕሮግራም ያትታል። በአብዮቱ መነሻ ወቅት “ከጠቅላላ የአገሪቱ ምርት የኢንዱስትሪ ምርት ከ15 በመቶ የማይበልጥ” እንደነበር የሚጠቁመው ሰነዱ፤ በዚህም ምክንያት በጊዜው የነበረው የሠራተኛው ቁጥር እና የትግል ልምድ “አነስተኛ” እንዲሆን አስገድዶት እንደነበር ያብራራል። 

እንዲያም ሆኖ ግን የሠራተኛው መደብ “ለረጅም የሥራ ሰዓት ጉልበቱን በርካሽ ለማፍሰስ መገደዱ፣ ገደብ ለሌለው ብዝበዛ መዳረጉ እና አንዳችም ዓይነት ዋስትና ያልነበረው መሆኑ” ሠርቶ አደሩ ጠንክሮ እንዲታገል እንዳደረገው የኢሠፓ ፕሮግራም ይተነትናል። የሠራተኛው መደብ በማህበር መልክ በመሰባሰብ ትግሉን ቢቀጥልም፤ “ለረጅም ጊዜ ተጓድሎበት ነበር” የተባለውን “የፓርቲ አመራር” ያገኘው ከኢሠፓ ምስረታ በኋላ መሆኑ በፕሮግራሙ ላይ ሰፍሯል። 

ይህን የፖለቲካ ፕሮግራም መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያን ለስድስት ዓመታት ያስተዳደረው ኢሠፓ፤ በአዋጅ መፍረሱ የተገለጸው በነሐሴ 1983 ዓ.ም ነበር። ኢሠፓ “ጸረ ዲሞክራሲ” እና “ወንጀለኛ ድርጅት” ተብሎ እንዲፈርስ የተደረገው፤ ከደርግ መንግስት መውደቅ ሶስት ወራት በኋላ በሽግግር መንግስቱ ወቅት በተቋቋመው የተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት በወጣ አዋጅ ነበር።  

“ሰላማዊ ሰልፍ እና ህዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ስነ ስርዓትን” በሚመለከት የወጣው ይህ አዋጅ “የኢሠፓና የደህንነት አባላት የተወካዮች ምክር ቤቱ ሌላ ውሳኔ እስካልወሰነ ድረስ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ ታግደዋል። ድርጅቶቹም ጸረ-ዴሞክራሲ እና ወንጀለኛ ድርጅቶች ስለሆኑ ፈርሰዋል” ሲል ደንግጓል። 

ይህ የአዋጁ ድንጋጌ፤ ኢሠፓን በድጋሚ ለማቋቋም የቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ ለማድረግ በምርጫ ቦርድ በምክንያትነት ቀርቧል። ኢሠፓን ያፈረሰው እና አባላቱንም ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ያገደው አዋጅ “አለመሻሩን” በማስረጃነት የጠቀሰው ምርጫ ቦርድ፤ “አሁንም ጸንቶ ባለ ህግ ወንጀለኛ ተብሎ ብያኔ ካረፈበት የፖለቲካ ድርጅት” ጋር የሚመሳሰል ስያሜ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንደማይችል ገልጾ ነበር። 

የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ የተሰኘውን ስያሜ በመያዝ ሀገር አቀፍ ፓርቲ በማቋቋም ሂደት ከተሳተፉት ውስጥ በኢሠፓ “በከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ ግለሰቦች” እንደሚገኙበት አደራጆቹ ከዚህ ቀደም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀው ነበር። ሆኖም አደራጆቹ የቀደሞዎቹን አመራሮች ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።  

ከደርግ መንግስት መውደቅ እና ኢህአዴግ የማዕከላዊ መንግስቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ አብዛኞቹ የኢሠፓ አመራሮች እና አባላት ለበርካታ ዓመታት መታሰራቸው ይታወሳል። የኢሠፓ ዋና ጸሐፊ እና የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስት ኃይለማርያምን ጨምሮ የተወሰኑ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችም ሀገሪቱን ጥለው በመውጣት ለስደት ተዳርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)