በኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ይደረጋል ተብሎ ስለሚጠበቀው ድርድር የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ምን አሉ?

በተስፋለም ወልደየስ

በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ውጊያ ለማስቆም ዋነኛ መሰናክል የሆነው፤ በተፋላሚ ወገኖች መካከል የተፈጠረው የመተማመን እጦት መሆኑን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ተናገሩ። አምባሳደር ማይክ ሐመር ይህን ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤን ለመሳተፍ ከሚገኙበት ኒውዮርክ፤ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 10፤ 2015 በቪዲዮ ኮንፍረስ በሰጡት መግለጫ ነው። 

እስካለፈው አርብ ድረስ አዲስ አበባ የነበሩት ልዩ ልዑኩ፤ በኢትዮጵያ በነበራቸው የ10 ቀናት ቆይታ ያከናወኗቸውን አበይት ተግባራት በተመለከተ አጠር ያለ ገለጻ ሰጥተዋል። የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ውጊያ በአፋጣኝ ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶችን ለማበረታት እንደነበር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

የአምባሳደር ሐመር ጉዞ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ባለስልጣናት፤ በአፍሪካ ህብረት በሚመራው የሰላም ንግግር ላይ እንዲሳተፉ የሚደረገውን ጥረት በተመሳሳይ የማበረታታት ዓላማ እንደነበረው መስሪያ ቤቱ ገልጿል። የአምባሳደር ሐመር የዛሬው ገለጻ፤ በእሁዱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ የተነሱትን አብዛኞቹን ጉዳዮች ያስተጋባ ሆኗል። 

“የእኔ የዲፕሎማቲክ ተሳትፎ የአፍሪካ ህብረትን ጥረት ወደፊት ለማራመድ ምን ማድረግ እንችላለን? የሚለውን በመረዳት ላይ በጣሙኑ ያተኮረ ነበር” ሲሉ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ በዛሬው መግለጫቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከትግራይ ክልል ተወካዮች እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት እና ከሌሎች የአሜሪካ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

ሐመር በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው እሁድ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ልዩ ልዑኩ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት፤ የሰላም ንግግሮችን ማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንዴት መስራት እንደሚቻል መምከራቸውን በዛሬው መግለጫቸው ተናግረዋል። 

የመንግስት ባለስልጣናቱ የተለያዩ ጉዳዮችን በተመለከተ ያነሷቸውን “አሳሳቢ ጉዳዮች” ማድመጣቸውንም አስረድተዋል። አምባሳደር ሐመር ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ተወካዮች ጋር በተነጋገሩበት ወቅት፤ ግጭት በማቆም ወዲያውኑ ወደ ሰላም ውይይት እንዲሄዱ በድጋሚ እንዳሳሰቧቸው ጠቅሰዋል። 

አርባ ሁለት ደቂቃ በወሰደው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ የዛሬ መግለጫ፤ የሰሜን ኢትዮጵያውን ውጊያ በተመለከተ ከጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል። በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ክልል ተወካዮች መካከል “በጅቡቲ ተካሄዶ ነበር” የተባለውን ውይይት በተመለከተ የቀረበላቸውን ጨምሮ፤ አምባሳደር ሐመር ለአብዛኞቹ ጥያቄዎች በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ አገላለጾችን ሲጠቀሙ ተደምጠዋል።

የትግራይ ኃይሎች በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ “ኤርትራ በሁሉም ግንባሮች ሰፊ ጥቃት ከፍታብናለች” ማለታቸውን አስመልክቶ ከአሜሪካው ፒ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ለቀረበ ጥያቄ፤ አምባሳደር ሐመር ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ይልቅ ድርጊቱን ማውገዙን መርጠዋል። በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ያለውን የኤርትራ ወታደሮች እንቅስቃሴ አሜሪካ እየተከታተለች መሆኑን የተናገሩት ልዩ ልዑኩ፤ ጉዳዩ “እጅግ አሳሳቢ ነው” ብለዋል። 

“ሁሉም የውጭ ተዋናዮች የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ማክበር እና ግጭቱን ከማቀጣጠል መቆጠብ ይኖርባቸዋል” ያሉት አምባሳደር ሐመር፤ “ከዚህ በበለጠ ግልጽ መሆን አንችልም። ይህንን በተደጋጋሚ ተናግረናል። ከአስመራ ጋር የቀጥታ ግንኙነት ለሚኖራቸው የምናሳስበው፤ ይህ ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆነ እና መቆም እንዳለበት ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ መገኘት ሊጠቅም የሚችለው ብቸኛው ነገር፤ ጉዳዮችን ማወሳሰብ እና አሳዛኙን ሁኔታ የበለጠ ማባባስ እንደሆነ ጠቁመዋል። አሜሪካ ጉዳዩን በተመለከተ ልትወስዳቸው የምትችላቸው “ሌሎች እርምጃዎች” ሊኖሩ እንደሚችሉ ዲፕሎማቱ በገደምዳሜ ቢገልጹም፤ ዝርዝር ጉዳዮችን በመግለጫቸው ከማንሳት ግን ተቆጥበዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ እየተሳተፉ ባሉ ወገኖች ላይ አሜሪካ ተጨማሪ ማዕቀብ የመጣል ሀሳብ እንዳላት ለተነሳው ጥያቄም አምባሳደር ሐመር ተመሳሳይ የምላሽ አሰጣጥ አካሄድ ተከትለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በውጊያው የሚሳተፉ ወገኖችን ወደ ሰላም ንግግር ለማምጣት በርካታ አማራጮችን በመመልከት ላይ መሆኗን የጠቆሙት ልዩ ልዑኩ፤ ከእነዚህ አማራጮች አንዱ ማዕቀብ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

“የማዕቀብ አማራጭ ሁሌም አለ። ማዕቀብ በሚገባቸው ላይ ማዕቀብ ለመጣል አናመነታም። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ዋነኛ ትኩረታችን የአፍሪካ ህብረት የሚያደርገው ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረት ነው” ብለዋል ሐመር። አሜሪካ እና ዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጭምር የሚሳተፉበት ይህ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፤ በአጭር ጊዜ ንግግር እንዲጀመር፣ ግጭት እንዲቆም እና እነዚህን ጉዳዮች በሰላም ለመፍታት የሚያስችል ከባቢ መፈጠሩን ማረጋገጥ እንደሆነ ልዩ ልዑኩ ጨምረው ገልጸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ እየተፋለሙ ያሉ ወገኖችን ወደ ንግግር ለመምራት አሜሪካ የቀራት “ተጽዕኖ መፍጠሪያ አማራጭ አለ ወይ?” የሚል ጥያቄም ለልዩ ልዑኩ ቀርቦላቸው ነበር። በተፋላሚ ወገኖች መካከል ንግግር እንዲጀመር ሀገራቸው በዲፕሎማሲው ረገድ በንቃት እየተሳተፈች እንደምትገኝ በምላሻቸው የጠቀሱት አምባሳደር ሐመር፤ ሆኖም የእያንዳንዱን ጥረቶቻቸውን ዝርዝር ለጋዜጠኞች ማጋራት እንደማይችሉ አስረድተዋል።

“በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፤ የምናደርገውን እያደረግን ያለነው [ተፋላሚ] ወገኖቹ የወደፊት አቅጣጫዎችን በውይይት የማግኘት ፍላጎት አላቸው በሚል ሙሉ እምነት ነው። ይህ ከዚህ በፊት በነበሩ ጊዜያትም ሆነ አዲስ አበባ በነበርኩ ጊዜ በምናደርጋቸው ጥረቶች የነበረ ነው። የሰላም ሂደቱን እንዴት መጀመር ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ከአፍሪካ ህብረት ጋር የምናከናውነውን ስራ በዚህ ሳምንትም እንቀጥላለን” ሲሉ አምባሳደር ሐመር የሀገራቸውን አቋም አብራርተዋል። 

በኒውዮርክ ዛሬ ከተጀመረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ሁኔታ የተመለከቱ ውይይቶች፤ ከአፍሪካ ህብረት እና ከሌሎች አካላት ጋር እንደሚያካሄዱም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አስታውቀዋል። “የአፍሪካ ህብረት የሰላም ሂደትን እንዴት ወደፊት ማራመድ ይቻላል?” በሚለው ላይ የሚደረገው ውይይት፤ ተፋላሚ ወገኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ ያስችላቸዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች መካከል “የመተማመን” ችግር እንዳለ የጠቆሙት አምባሳደር ሐመር፤ የዚህ ሳምንት ውይይቶች ይህን በመፍታት ረገድ የራሳቸው ሚና እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል። የመተማመን እጦት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ውጊያ ለማስቆም ዋነኛ መሰናክል መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ በውጊያ ላይ ያሉ ኃይሎችን “በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ባሉ ሁለት ወገኖች” የመሰሉት አምባሳደር ሐመር፤ በቤተሰቦች መካከል የሚኖር ጸብ “በጣም አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አዳጋች የሆነበትን ምክንያት በምሳሌ ለማስረዳት ሞክረዋል።

ተፋላሚ ወገኖች አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ያላቸውን መተማመን ለመገንባት ዕድል መስጠት እንደሚገባቸው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በዛሬው መግለጫቸው አሳስበዋል። በሁለቱም ወገኖች በቂ እምነት ማሳደር ከተቻለ፤ ውጊያ ማቆም ወደሚያስችሉ ሂደቶች ደረጃ በደረጃ መሸጋገር እንደሚቻል ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ የተደረገውን እና በህወሓት በኩልም ተቀባይነት አግኝቶ ወደነበረው፤ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ወደ ማቆም ውሳኔ መሸጋገር እንደሚቻልም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)